አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ አደረጉ
በሰሜን ኮሪያ ድንበር አቅራቢያ የተደረገው ልምምድ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች፣ የውጊያ ጄቶች፣ ድሮኖች እና ታንኮች ተሳትፈዋል
ፒዬንግያንግ ለሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ልምምድ አፃፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች
አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በዛሬው እለት በአይነቱ የተለየና ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸው ተነገረ።
በልምምዱ 2 ሺህ 500 ወታደሮች፣ የውጊያ ጄቶች፣ ሄሊኮፕተሮች፣ ድሮኖች፣ ታንኮችና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ተሳትፈዋል ተብሏል።
የተኩስ ልምምዱ ደቡብ ኮሪያን ከሰሜን ኮሪያ በሚያዋስናት ድንበር በቅርብ ርቀት መካሄዱ ተገልጿል።
ሀገራቱ በ2017 አድርገውት ከነበረውና ከ250 በላይ የጦር መሳሪያዎች ከተሞከሩበት የጋራ ልምምድ በሶስት እጥፍ የሚበልጠው የዛሬው ልምምድ ፒዬንግያንግን አስቆጥቷል።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያም አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ያደረጉትን ወታደራዊ ልምምድ "ፒዬንግያንግን ለመውረራ የሚደረግ ዝግጅት ነው" ብሎታል።
ኪም ጆንግ ኡን ከዚህ ቀደም ተቃውሟቸውን ሚሳኤል በመተኮስ በማሳየታቸው ከሰሞኑም የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት ሊያባብስ የሚችል እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ የፈረንጆቹ 2022 ከገባ ወዲህ ከ100 ሚሳኤሎችን መተኮሷን ያወሳው ዘገባው፥ የኒዩክሌር መርሃግብሯን አጠናክራ ገፍታበታለች ብሏል።
ባለፈው ወር በአሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዬን ሱክ የልም የፒዬንግንግን ስጋትነት የሚቀንስ ወታደራዊ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
አሜሪካ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ተሸካሚዋንና በኒዩክሌር የምትንቀሳቀስ መርከቧንም ወደ ደቡብ ኮሪያ መላኳ የሚታወስ ነው።
ከዚህ ቀደም አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያና ጃፓን ጋር የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድ አጥብቃ ያወገዘችው ሰሜን ኮሪያ ለዛሬው ልምምድ እስካሁን ሚሳኤል አልተኮሰችም።