በደቡብ ኮሪያ ሴኡል በሀሎዊን ክብረ በዓል ላይ ከ150 በላይ ሰዎች ሞቱ
ሴኡል ከተማ የሀሎዊን በዓል ላይ በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ የሰዎች ህይወት አልፏል
በሴዑል መገፋፋትና መረጋገጥ አደጋ ከሞቱት መካከል 19ኙ የውጭ ሀገራት ዜጎች ናቸው
በደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል ከተማ ሀሎዊን የተባለ ክብረ በዓል በማበክር ላይ በነበሩ ሰዎች መካከል በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ 151 ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ።
አደጋው የደረሰው በዓሉን በማክበር ላይ የነበሩ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በታዋቂው ኢታወን የምሽት ህይወት መዝናኛ ወደሚገኝ ጠባብ ጎዳና ሲገቡ እንደሆነ ተነግሯል።
በዚህም የ151 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ100 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች አብዛኞቹ ታዳጊዎች እና በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆኑም ተነግሯል።
በተጨማሪም በመረጋገጥና በመገፋፋት አደጋው ከሞቱ ሰዎች መካከል 19 ሰዎች የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው መሆኑን የደቡብ ኮሪያ የአደጋ ጊዜ ባልስልጣናት አስታውቀዋል።
በአገዳው ህይወታቸው ካለፈው እና ከተጎዱ ሰዎች በተጨማሪም ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ጠፍተውብና በሚል ቤተሰቦቻው እንዳስመዘገቡምደቡብ ኮሪያ አስታውቃለች።
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዬኡል አደጋው የደረሰበትን ስፍራ የጎበኙ ሲሆን፤ የአደጋውን መንስዔ የሚመረምር እና ለተጎጂዎች ድጋፍ የሚያደርግ ቡድን እንዲዋቀርም አዘዋል።
ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዬኡል በሀገሪቱ ብሄራዊ የሀዘን ቀን ማወጃቸውን ተነግሯል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑዔለ ማክሮንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በአደጋው ማዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ከደቡብ ኮሪያ ጎን መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሰዎች ፊታቸው ላይ የተለያዩ አስፈሪ ጭምብሎችን እና ቀለማትን በመቀባት የሚያከብሩት ሀሎዊን ኮቪድ 19 ከተከሰተ በኋላ በደቡብ ኮሪያ ሲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በዚህም ምክንያት በርካቶች በዓሉን ለማክበር ሳይወጡ እንዳልቀረም ተነግሯል።