ደቡብ ኮሪያ፤ ፒዮንግያንግ ሚሳይል ማስወንጨፏን ተከትሎ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ጣለች
ሰሜን ኮሪያ ሀውሶንግ-18 የተባለ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይል ሙከራ አድርጋለች
የሰሜን ኮሪያ ጦር ጄኔራልን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል
ደቡብ ኮሪያ በአራት የሰሜን ኮሪያ ግለሰቦች እና በሦስት አካላት ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ሴኡል ፒዮንግያንግ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፏን ተከትሎ የአንድ ወገን ማዕቀብ መጣሏን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ አስታውቋል።
እርምጃው ሰሜን ኮሪያ ሀውሶንግ-18 የተባለ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይል ሙከራ ካደረገች ከሁለት ቀናት በኋላ የተወሰደ ነው።
የፒዮንግያንግ ሰሞነኛ ሙከራ ዓለም አቀፍ ውግዘት ገጥሞታል።
"የሰሜን ኮሪያ የረጅም እርቀት የባላስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፍ የኮሪያ ልሳነ ምድርን እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ምላሽ ለመስጠት የኒውክሌር ልማትና የገንዘብ ድጋፍ በሚያቀርቡ አራት ግለሰቦች እና ሦስት ድርጅቶች ላይ የአንድ ወገን ማዕቀብ እንዲጣል ተወስኗል" ሲል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
አራቱ ግለሰቦች የሰሜን ኮሪያ ጦር ጄኔራል ፖለቲካ ቢሮ ዳይሬክተር ጆንግ ኪዮንግ-ታክን ጨምሮ የቀድሞ እና የአሁን ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካትታሉ።
ሦስቱ አካላት በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ በግንባታ ንግድ ላይ የተሰማራው የሰሜን ኮሪያ የንግድ ድርጅትንና ሌሎችንም ያጠቃልላል ሲል ሚንስቴሩ አስታውቋል።