ኤምሬትስ እና ደቡብ ኮሪያ በኒዩክሌር ሃይል፣ በኢንቨስትመንት እና ወታደራዊ ዘርፎች ትስስራቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ነው
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ለይፋዊ ጉብኝት አቡ ዳቢ ገብተዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንም ለፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ዮን በቃስር አል ዋታን ቤተመንግስት የክብር አቀባበል እንደተደረገላቸውም ነው የኤምሬትስ ዜና አገልግሎት ዋም የዘገበው።
ደቡብ ኮሪያ ከድፍድፍ ነዳጅ ፍላጎቷ 10 በመቶውን የምታገኘው ከኤምሬትስ ነው።
ኤምሬትስም ቢሊየን ዶላሮችን የሚያወጡ የደቡብ ኮሪያ ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ከሴኡል ታስገባለች።
ጠንካራ ግንኙነት የመሰረቱት ሁለቱ ሀገራት በኒዩክሌር ሃይል፣ በኢንቨስትመንት እና ወታደራዊ ዘርፎች ትስስራቸውን ለማጠናከር የፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ጉብኝት ትልቅ ድርሻ አለው ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የደቡብ ኮሪያውን ፕሬዚዳንት እንደተቀበሉ፥ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሴኡል የ30 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ለመጀመር ማቀዷን መናገራቸውን የደቡብ ኮሪያው የዜና ወኪል ዮናፕ ዘግቧል።
ዘገባው ኤምሬትስ በየትኞቹ ዘርፎች መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላት ግን አልጠቀሰም።
ፕሬዚዳንይ ዮን በአቡ ዳቢ ቆይታቸው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነትን ከኤምሬትስ አቻቸው ጋር እንደሚፈራረሙም ዮናፕ ስማቸውን ያልጠቀሳቸውን ባለስልጣናትን ጠቅሶ አስነብቧል።
ደቡብ ኮሪያ በ2022 ለኤምሬትስ ኤም ሳም የተሰኘውን ዘመናዊ ጸረ ሚሳኤል በ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ለመሸጥ መስማማቷ የሚያወስ ነው።
አቡ ዳቢ በኢራን ከሚደገፉ የየመን ሃውቲ ታጣቂዎች ሊቃጡ የሚችሉ የድሮን ጥቃቶችን ለመመከት በትኩረት እየሰራች መሆኑን ስትገልጽ ቆይታለች።
ደቡብ ኮሪያ በ20 ቢሊየን ዶላር በምዕራባዊ የኤምሬትስ በርሃ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ለመገንባት ማቀዷን አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው አውስቷል።
ይህ ፕሮጀክት የአቡ ዳቢን ሩብ የሃይል ፍላጎት እንደሚሞላ የሚጠበቅ መሆኑም የሀገራቱን ትብብር ይበልጥ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።