ወንዶች ራሳቸውን እንዲያጠፉ ምክንያቱ ሴቶች ናቸው ያሉት ፖለቲከኛ ከፍተኛ ትችት ቀረበባቸው
ከፍተኛ ራስን የማጥፋት ምጣኔ በሚገኝባት ደቡብ ኮርያ 77 በመቶዎቹ ሟቾች ወንዶች ናቸው
ፖለቲከኛው በማህበረሰቡ ውስጥ የሴቶች የበላይነት መጨመር ወንዶች ራሳቸውን እንዲያጠፉ ዋነኛ ምክንት ነው ብለዋል
ወንዶች ራሳቸውን እንዲያጠፉ ምክንያቱ ሴቶች ናቸው ያሉት ፖለቲከኛ ከፍተኛ ትችት ቀረበባቸው።
የሴቶች የበላይነት መጨመር የወንዶች ራስን ማጥፋት እንዲጨምር ምክንይት ሆኗል ያሉት የደቡብ ኮርያ ፖለቲከኛ ከፍተኛ ትችትን እያስተናገዱ ነው፡፡
የሴኡል ከተማ ምክር ቤት ተመራጭ የሆኑት ኪሚ ኪዱክ የተባሉት ፖለቲከኛ በምክር ቤቱ በሰጡት ያልተረጋገጠ ሀሳብ የሴት መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ነቀፌታ እየቀረበባቸው ሲሆን ከምክር ቤት አባልነታቸውም እንዲነሱ ተጠይቋል፡፡
በማህበረሰብ ውስጥ ፣ በስራ ቦታዎች እና በውሳኔዎች ላይ የሴቶች የበላይነት መጨመር ወንዶች እንዲጨነቁ እና ስራ የሌላቸው ወንዶች ደግሞ ስራ ባላት ሴት በትዳር አጋርነት አለመፈለጋቸው ጭንቀት ውስጥ ከቷቸዋል ብለዋል ኪም፡፡
ፖለቲከኛው ይህን ቢሉም ከፍተኛ የጾታዊ እኩልነት ክፍተት በሚገኝባት ደቡብ ኮርያ ሴቶች በሙሉ ሰአት ስራዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ከወንዶች አኩል አይደለም፤ ይለቁንም ቋሚ ባልሆኑ እና በትርፍ ሰአት በሚሰሩ ስራዎች ላይ በብዛት ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
በክፍያ ደረጃም ቢሆን ሴቶች ለተመሳሳይ ስራ የሚከፈላቸው ደሞዎዝ ከወንዶች በ29 በመቶ ያነሰ ነው፡፡
የአዕምሮ እና የስነልቦና ሀኪሞች የፖለቲከኛውን ሀሳብ ከነቀፉ መካከል ሲሆኑ የወንዶች ራስን የማጥፋት ምጣኔ ከፍተኛ መሆን አለምአቀፋዊ እውነታ ነው ብለዋል፡፡
ከ50 አመት አድሜ በታች ያሉ ወንዶች በከፍተኛ መጠን ራሳቸውን የሚያጠፉባትን ብሪታንያን ለአብነት ያነሱት ሀኪሞቹ የወንዶች ሞት ከሴቶች የበላይነት ጋር የሚገኛኝ አይደለም ነው ያሉት፡፡
ቢሆን እንኳን በሳይንሳዊ መንገድ በጥናት ያልተረጋገጠ ሀሳብ በምክር ቤት አባላት መሰንዘሩ ህብረተሰቡ በአስተዳደር እና ፖሊሲዎች ላይ እምነት እንዲያጣ የሚያደርግ ነው ሲሉ ሃሳቡን ተችተዋል፡፡
ከፍተኛ የራስ ማጥፋት ከሚፈጸምባቸው ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ደቡብ ኮሪያ ከሟቾች መካከል 77 በመቶውን የሚሸፍኑት ወንዶች ናቸው፡፡
በሀገሪቱ በ2018 ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች ቁጥር 430 ሲሆን በ2023 ይህ ቁጥር ከአንድሺ ተሻግሯል፡፡
የፖለቲከኛውን ሀሳብ የተቃወሙ የሴቶች መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጉዳዩን በኤክስ(ትዊተር) ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ እየተነጋገሩበት ሲሆን፤ የምክር ቤት አባሉ ለሰነዘሩት ሀሳብ በዛው ምክር ቤት ውስጥ ሴቶችን ይቅርታ እንዲጠይቁ ከምክር ቤት አባልነታቸውም እንዲነሱ ቁጣቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡