የደቡብ ኮሪያ ህግ አውጪዎች ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን እንዲነሱ በአብላጫ ድምጽ ወሰኑ
ፕሬዝዳንቱ ስልጣናቸውን የሚቀሙት የሀገሪቱ ህገ መንግሥት ፍርድ ቤት ከወሰነ ብቻ ነው
ፕሬዝዳንት ዩን እስከ መጨረሻው እንደሚፋለሙ ዝተዋል
የደቡብ ኮሪያ ህግ አውጪዎች ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን እንዲነሱ በአብላጫ ድምጽ ወሰኑ።
የሰለጠነ የዲሞክራሲ ባህል አካት የምትባለው እስያዋ ሀገር ደቡብ ኮሪያ በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ ነች።
አለመረጋጋቱ የመጣው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዬኦል ሀገሪቱ ከሰሜን ኮሪያ እና ከጸረ መንግሥት አካላት የደህንነት ስጋት ተደቅኖባታል በሚል የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት አዋጅ ማወጃቸውን ተከትሎ ነው።
የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሻረ ቢሆንም ይህ በቂ አይደለም በሚል ከስልጣን እንዲነሱም በአብላጫ ድምጽ ውሳኔ አስተላልፏል።
ዛሬ በተካሄደው በዚህ ውሳኔ መሰረት ፕሬዝዳንት ዩን ከስልጣናቸው እንዲነሱ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ተከትሎ ውሳኔው በፍርድ ቤት እስከሚጸድቅ ድረስ ስልጣናቸው በግማሽ ተገድቧል።
በዚህም መሰረት የፖለቲካ ትግሉ የቀጠለ ሲሆን በተለይም አሁን ሽኩቻው ከምክር ቤት ወደ ፍርድ ቤት ዞሯል።
የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት ውሳኔ በፍርድ ቤት የሚጸና ከሆነ በስድስት ወራት ውስጥ አዲስ የፕሬዝዳንት ምርጫ ይካሄዳል ተብሏል።
የፕሬዝዳንቱ ከስልጣን ይነሱ ውሳኔ በሀገሪቱ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት የመጨረሻ እልባት እስከሚያገኝ ድረስ ጠቅላይ ሚንስትር ሀን ደክ ሱ የደቡብ ኮሪያ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው እንደሚያገለግሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ዩን በምክት ቤት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ለስልጣናቸው እስከ መጨረሻው እንደሚፋለሙ ተናግረዋል።
ደቡብ ኮሪያ በህገመንግስት ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷን ከስልጣን የማንሳት ሂደት ስትካሂድ የአሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም።
በ2017 የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ፓርክ ዩን ሀን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተው ከስልጣን ተነስተው ነበር።