ደቡብ ኮሪያ ለአረጋውያን ዜጎቿ የምትሰጠው ነጻ የባቡር ጉዞ የፖለቲካ ራስ ምታት ሆኗል ተባለ
የደቡብ ኮሪያ ህዝብ በፍጥነት እያረጀና የምድር ባቡር አገልግሎት ዋጋ መጨመር ውጥረት ከፍቷል
ከ51 ሚሊዮኑ የደቡብ ኮሪያ ህዝብ 18 ከመቶ በላዩ 65 ዓመትና ከዚያ በላይ ነው
ደቡብ ኮሪያ ለአረጋውያን ዜጎቿ የምትሰጠው የባቡር ጉዞ የፖለቲካ ራስ ምታት ተባለ።
ሴኡል ላለፉት አራት አስርት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 65 ዓመትና እና ከዚያ በላይ ለሆኑ አረጋዊያን ዜጎቿ ነጻ የባቡር ጉዞን ፈቅዳለች።
ይህም ሀገሪቷ አረጋውያን በንቃት እንዲቀሳቀሱ በማድረግ ስሟ በበጎ እንዲነሳ አድርጓል።
አረጋዊያንም ይህን እድል በመጠቀም በተለይም ቁሳቁስና ምግቦችን በማድረስ አገልግሎት ተሰማርተዋል ነው የተባለው።
ሆኖም ይህ የነጻ ጉዞ የደቡብ ኮሪያ ህዝብ በፍጥነት እያረጀና የምድር ባቡር አገልግሎት ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ ትልቅ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኗል።
በአጠቃላይ ይህን የአረጋዊያን ጥቅም ስለማስወገድ የታሰበ ነገር ባይኖርም አንዳንድ ከተሞች የሀገሪቱ መንግስት የተወሰነውን ወጪ ካልሸፈነ ከፍተኛ የሆነ የታሪፍ ጭማሪ አሊያም የተጠቃሚነት የእድሜ ጣሪያን ከፍ ለማድረግ እየዛቱ ነው ተብሏል።
ሮይተርስ እንደዘገበው የደቡብ ኮሪያ ገንዘብ ሚንስቴር ይህን አጥብቆ ይቃወማል።
አለመግባባቱ ዋጋ እየጨመረ ባለበት የእስያ አራተኛ ትልቅ የምጣኔ-ሀብት ባለቤት በሆነችው ደቡብ ኮሪያ፤ የሰፊ ፈተናዎች አካል ነው ተብሏል።
በሀገሪቱ በ24 ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሸማቾች ደስተኛ አይደሉም።
አንዳንድ የገዢው ፓወር ፓርቲ አባላት ለአዛውንቶች የምድር ባቡር ጥቅማጥቅሞች መነሳት በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የፓርላማ ምርጫ እድላቸውን እንደሚያጠብ አስጠንቅቀዋል።
ከ51 ሚሊዮኑ የደቡብ ኮሪያ ህዝብ 18 ከመቶ በላይ የሚሆነው እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ ነው።
በሀገሪቱ የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሰረት ይህ መጠን በፈረንጆች 2035 30 በመቶ እና በ2050 ደግሞ 40 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።