አሜሪካ ግዙፍ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኗን ወደ ደቡብ ኮሪያ ላከች
ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል በተኮሰች ማግስት አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የአየር ሃይል የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ጀምረዋል
አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የአየር ሃይል የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት አባብሶታል
አሜሪካ ቢ -1ቢ የተሰኘውን ግዙፍ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኗን ወደ ደቡብ ኮሪያ ልካለች።
ዋሽንግተን ኤፍ 16 ተዋጊ ጄቶችንም ወደ ሴኡል መላኳ ተሰምቷል። የአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የጦር አውሮፕላኖች የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ዛሬ ተጀምሯል።
ሀገራቱ ልምምዱን የፈረጠመ አቅማቸውን ማሳያ አድርገው ይጠቀሙበታል ነው የተባለው።
የሀገራቱ የጋራ ወታደራዊ ማዘዣ ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው፥ የደቡብ ኮሪያ ኤፍ 35ኤ ጄቶች በአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ታጅበው ልምምዳቸውን እያደረጉ ነው።
በዚህ ልምምድ የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ አቅም በጉልህ ታይቷል፤ ዋሽንግተን የኮሪያ ልሳነምድርን ውጥረት ለማርገብ ቁርጠኝነቷንም አሳይታለች ይላል መግለጫው።
ሀገራቱ የሰሜን ኮሪያን እንቅስቃሴ በቅርበት ለመከታተልና ለፀብ አጫሪ ድርጊቷም ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውም ነው በመግለጫው የተነሳው።
ሰሜን ኮሪያ ህዋሶንግ 17 የተሰኘውን አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳኤል በትናንትናው እለት ሞክራለች።
የኒዩክሌር አረር መሸከም የሚችለው ህዋሶንግ እስከ 15 ሺህ ኪሎሜትሮች የመጓዝ አቅም እንዳለው ተነግሯል።
የኪም ጆንግ ኡን ሀገር አሜሪካ ጎረቤቶቿን ደቡብ ኮሪያና ጃፓን አጋር ለማድረግ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ሚሳኤል በማስወንጨፍ እየገለፀች ነው።
ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ የጀመሩትን ወታደራዊ ልምምድ እንደ ጦርነት ሰበቃ የተመለከተችው ፒዮንግያንግ፥ ወደ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ሚሳኤል ተኩሳለች።
አሜሪካ መድረስ ይችላል የተባለውን አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል መሞከር መጀመሯም የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት ይበልጥ ጨምሮታል።
አሜሪካ በቅርቡ ሰሜን ኮሪያ ከሚሳኤል ማስፈራሪያዋ ካልታቀበች ለደቡብ ኮሪያና ጃፓን ኒዩክሌር እስከማስታጠቅ እደርሳለሁ ማለቷ ይታወሳል።
ዋሽንግተን የቀጠናው አጋሮቿን በካምቦዲያ ካወያየች በኋላ የመጀመሪያ የሆነው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ከወደ ፒዬንግያንግ የሚሳኤል ምላሽን እንዳያስከትል ተሰግቷል።