ፑቲን ለሰሜን ኮሪያው መሪ ያበረከቱላቸው ሶስት ስጦቻዎች ምንድን ናቸው?
በሰሜን ኮሪያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ቭላድሚር ፑቲን ለኪም ጆንግ ኡን ሶስት ስጦታዎችን አበርክተውላቸዋል
ፑቲን በዛሬው እለት ሩሲያ በዩክሬን ለምታካሄደው ጦርነት ሙሉ ድጋፍ ወደሰጠችው ሰሜን ኮሪያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል
በሰሜን ኮሪያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ቭላድሚር ፑቲን ለኪም ጆንግ ኡን ሶስት ስጦታዎችን አበርክተውላቸዋል።
ፑቲን፣ ሩሲያ ሰራሽ ዘመናዊ አውረስ ሊሞዚን፣ የሻይ መጠጫ እቃዎች እና አድሚራል ድሪክ ለኪም ማበርከታቸውን ሮይተርስ የሩሲያውን ዜና አገልግሎት ታስን ጠቅሶ ዘግቧል።
በሰሜን ኮሪያ በጉብኝት ላይ ያሉት ፑቲንም በምላሹ የእሳቸውን ምስል ያሉበትን ቅርጽ መቀበላቸውን የፕሬዝደንቱ አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ ተናግረዋል።
ፑቲን በዛሬው እለት ሩሲያ በዩክሬን ለምታካሄደው ጦርነት ሙሉ ድጋፍ ወደሰጠችው ሰሜን ኮሪያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
አውረስ ሊሞዚን፣ በሶቬት ጊዜ የነበረው ዚል ሊሞዚን ማሻሻያ ተደርጎበት የተሰራ ዘመናዊ መኪና ሲሆን ፕሬዝደንት ፑቲን ባለፈው ግንቦት ወር በተካሄደው በዓለ ሲመታቸው ላይ ያሽከረከሩት መኪና አይነት ነው።
ባለፈው መስከረም ወር ኪም ምስራቃዊ ሩሲያን በጎበኙበት ወቅት፣ ፑቲን ብረት ለበስ የሆነውን አውረስ መኪና አሳይተዋቸው ነበር። ኪም በመኪናው ውስጥ ከፑቲን ጋር ቁጭ ብለው የተደሰቱ ይመስሉም ነበር።
ባለፈው የካቲት ወር ፑቲን አውረስ ሊሞዚንን ለኪም የሰጡ ሲሆን የአሁኑ ስጦታ ሁለተኛ ነው፤ ይህ ማለት ኪም ቢያንስ ሁለት አውረስ ሊሞዚን አላቸው ማለት ነው።
ኪም የዘመናዊ መኪና አድናቂ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። ኪም በርካታ ቅንጡ መኪና እንዳላቸው ይነገራል። የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የቅንጦት እቃዎች ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዳይገቡ እግድ ስለጣለ እነዚህ መኪኖች በህገወጥ መልኩ ሳይገቡ እንዳልቀረም ይገለጻል።
ኪም በማይባች ሊሞዚን፣ በመርሲዴስ፣ በሮል ሮይስ ፓንቶም እና በሌክሰስ ስፓርትስ ዩቲሊቲ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ታይተዋል።
አንድ ከፍተኛ የሩሲያ ባለስልጣን እንደገለጹት ከሆነ ሩሲያ ሴንትፒተርስበርግ ውስጥ በሚገኘው የቀድሞው የቶዮታ ፋብሪካ ውስጥ አውረስ የተባለውን ዘመናዊ መኪና ማምረት ጀምራለች።
ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ያላችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተች ወዲህ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት በይፋ እያጠናከረች ነው።
አሜሪካ እና ምዕራባውያን ሀገራት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በስጋት ያዩታል።
ምዕራባውያን ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን ለምታደርጠው ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውል የጦር መሳሪያ ታቀርባለች ሲሉ ይከሷታል። ሰሜን ኮሪያ ግን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ነው በማለት በተደጋጋሚ አጣጥላዋለች።