የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ከትራምፕ መመረጥ በኋላ የጎልፍ ጨዋታ ልምምድ ጀመሩ
ዩን ሱክ የል ከሰሞኑ ከስምንት አመት በኋላ ወደ ጎልፍ መጫወቻ ስፍራ በማቅናት ልምምድ የጀመሩት በቀጣይ ከትራምፕ ጋር ሲገናኙ ለመጫወት ነው ተብሏል
የአሜሪካው አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው የሁለቱን ኮሪያዎች ውጥረት ለማርገብ መሞከራቸው ይታወሳል
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል የጎልፍ ጨዋታ ልምምድ ማድረግ ጀመሩ።
ፕሬዝዳንቱ ወደ ጎልፍ መጫወቻ ስፍራ በማቅናት ልምምድ የጀምሩት በ2024ቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ነው።
የፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫም ፕሬዝዳንቱ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ጎልፍ መጫወቻ ስፍራ ያቀኑት ከስምንት አመት በፊት በ2016 እንደነበር ገልጿል።
“በርካታ ለትራምፕ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እኔና ትራምፕ በአጭር ጊዜ የምንግባባ እንደሆንን ይነግሩኛል” ያሉት ፕሬዝዳንት ለተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ስልክ ደውለው ደስታቸውን ገልጸውላቸዋል።
ትራምፕ “ማራላጎ” በተሰኘውና ፍሎሪዳ በሚገኘው ቅንጡው መዝናኛ እና መኖሪያቸው ውስጥ ጎልፍ እንደሚያዘወትሩ ይታወቃል።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ከስምንት አመት በኋላ ወደ ጎልፍ ልምምድ ስፍራ መመለስም ትራምፕ በሴኡል ጉብኝት ሲያደርጉም ሆነ እርሳቸውም ወደ አሜሪካ ለጉብኝት ሲያቀኑ አብረው ለመጫወት ያለመ ነው ተብሏል።
ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማጠናከር ከትራምፕ ጋር ጓደኛ መሆን እንደ አንድ መሳሪያ ለመጠቀም ያሰቡት ዮን ሱክ የል ከሪፐብሊካኖች ጋር የሀገራቱን ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እየመከርን ነው ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
አሜሪካ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች ዋነኛ የንግድ ማዕከል መሆኗ ይታወቃል። በመጀመሪያው የትራምፕ የስልጣን ዘመን (ከ2017 እስከ 2021) በደቡብ ኮሪያ የሚገኙ 28 ሺህ 500 የአሜሪካ ወታደሮች ወጪ መጋራት ጉዳይ ሀገራቱን በተደጋጋሚ ሲያጋጭ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ትራምፕ በ2019 የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና የወቅቱን የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሙን ጃይ ኢን በሁለቱ ኮሪያዎች ከጦርነት ነጻ ቀጠና (ዲኤምዜድ) በማጨባበጥ የኮሪያ ልሳነ ምድርን ለማረጋጋት ታሪካዊ ሙከራ አድርገዋል።
በትራምፕ የተጀመረው ጥረት ሳይገፋበት ቀርቶ በባይደን አስተዳደር የሀገራቱ ውጥረት ተባብሶ ቀጥሏል።
አሜሪካ ወደ ደቡብ ኮሪያ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች እና የጦር ጄቶችን መላክና ከሴኡል እና ቶኪዮ ጋር የሶስትዮሽ ወታደራዊ ልምምድ ስታደርግ ቆይታለች።
ፒዮንግያንግ በአንጻሩ የሶስትዮሽ ልምምዱ የጦርነት ዝግጅት ነው በሚል ተቃውሞዋን ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ መግለጿን ቀጥላለች።
ትራምፕ የተመረጡበት ምርጫ በሚካሄድበት እለት ያደረገችው አሜሪካ የሚደርስ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራም አዲሱ ፕሬዝዳንት የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን የሚያባብስ እርምጃ እንዳይወስዱ ለማስጠንቀቅ ያለመ ነበር ተብሏል።
ለትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን ያደረሱት ኪም ጆንግ ኡን ሀገራቸው የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ይሻሉ።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል በበኩላቸው ከትራምፕ ጋር ጎልፍ ሲጫወቱ የፒዮንግያንግ የኒዩክሌርና ሚሳኤል ፕሮግራምን ለመግታት ጠንከር ያለ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ለማግባባት እንደሚሞክሩ ይጠበቃል።