የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ህግ "መፈንቅለ መንግስት" ወይስ "የሰሜን ኮሪያ ሴራ መበጠሻ"?
ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ወታደራዊ ህግ እንዲያውጁ ምክር ለግሰዋቸዋል የተባሉትን የመከላከያ ሚኒስትር ከስልጣናቸው አንስተዋል

የፕሬዝዳንቱን ያለመከሰስ መብት ለማስነሳት ቅዳሜ በፓርላማ ድምጽ ይሰጣል
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል የመከላከያ ሚኒስትራቸውን ኪም ዮንግ ዩን ከስልጣን አነሱ።
የፕሬዝዳንት ዮን ጽህፈት ቤት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ በሳኡዲ አረቢያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር የሆኑት ቾይ ዩንግ ዩክ አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር እንዲሆኑ መመረጣቸውን አመላክቷል።
ከስልጣናቸው የተነሱት ኪም ዮንግ ዩን ፕሬዝዳንት ዮን ለስድስት ስአታት የቆየውንና ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳውን ወታደራዊ ህግ እንዲያውጁ መምከራቸው ተገልጿል።
ዴሞክራቲክ ፓርቲ እና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሬዝዳንቱ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ በህግ እንዲጠየቁ ያስገቡት ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ የሀገሪቱ ፓርላማ የፊታችን ቅዳሜ ድምጽ እንደሚሰጥበት አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሰሜን ኮርያ ጋር አደገኛ ሴራ እየሸረቡ ነው በሚል ሀገሪቱ በወታደራዊ እዝ እንድትመራ ውሳኔ እንዳሳለፉ ወታደሮች ከሄሊኮፕተሮች ወርደው፤ መስኮቶችን ሰባብረው ወደ ሀገሪቱ ፓርላማ ህንጻ ዘልቀው መግባታቸው የሚታወስ ነው።
"ሁሉም ወታደሮች ድርጊቱን የፈጸሙት በእኔ ትዕዛዝ ነው፤ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ" ያሉት ኪም፥ ለተፈጠረው ትርምስ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ሚኒስትሩ ወታደራዊ ህጉ በታወጀ ቅጽበት ያሳለፉት ውሳኔ "በራስ ላይ የሚታወጅ መፈንቅለ መንግስት" ይመስላል የሚሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፥ የሰሜን ኮሪያ ጉዳይ እንደ ሽፋን መቅረቡን ያምናሉ።
በህጋዊ መንገድ ስልጣን ከያዙ በኋላ በስልጣን ለመቆየት ጦርነት በሌለበት ወቅት የወታደራዊ ህግ በማውጣትና ከሲቪል ይልቅ ወታደራዊ አገዛዝን መምረጥ መንግስትን መገልበጥ መሆኑን በመጥቀስም፥ የወታደራዊ ህጉ ዋነኛ አላማ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ማስቆም እንደነበር ይገልጻሉ።
ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ዴሞክራት ከተሻረው የወታደራዊ ህግ በተያያዘ በርካታ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና አቃቤያነ ህግ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል።
ገዥው “ፒፕል ፓወር ፓርቲ" ግን ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የልን ከስልጣን ለማንሳትና ያለመከሰስ መብታቸውን ለማንሳት ቅዳሜ በሚደረገው የፓርላማ ስብሰባ አዳራሽ ለቆ ለመውጣት አልያም የተቃውሞ ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀቱን ነው ያስታወቀው።
የቀረበው ሞሽን እንዲጸድቅ ከምክርቤቱ 300 አባላት ሁለት ሶስተኛው ወይም 200 የሚሆኑት ድጋፍ መስጠት ይኖርባቸዋል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በድምሩ 192 መቀመጫዎች አላቸው።
በቅዳሜው ድምጽ አሰጣጥም የፕሬዝዳንቱን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት ቢያንስ ከራሳቸው ፓርቲ ስምንት ሰዎች እና ሁሉም ተቃዋሚዎች የድጋፍ ድምጽ መስጠት ይኖርባቸዋል።
ዮን ያለመከሰስ መብታቸው በምክርቤት ከተነሳ የህገመንግስታዊ ፍርድቤት ከስልጣናቸው ይነሱ ወይስ አይነሱ በሚል ውሳኔ እስኪያሳልፍ ድረስ ይታገዳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃን ዱክ ሶ የፕሬዝዳንቱን ሃላፊነቶች ተክተው ይሰራሉ።