“ደቡብ ሱዳን መሬቶቿ ኢትዮጵያን ለመጉዳት እንዲውሉ አትፈቅድም”- የደቡብ ሱዳን የሃገር ግዛት ሚኒስትር
ደቡብ ሱዳን “በብሔራዊ ውይይት ስም የአገዛዝ ለውጥ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት” እንደማትቀበልም ገልጸዋል
“ህወሓት በስልጣን ላይ እያለ ተራማጅ መስሎ ቢታይም ጎጠኛ እና ተገንጣይ መሆኑን ማረጋገጡ ያሳዝናል”ም ነው ሚኒስትሩ ያሉት
ደቡብ ሱዳን መሬቶቿ ኢትዮጵያን ለመጉዳት እንዲውሉ አትፈቅድም ሲሉ የደቡብ ሱዳን የሃገር ግዛት ሚኒስትር ፖል ማዮም አኬች ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት በጁባ ከኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል መሃዲ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡
በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ከስርዓት እና ግለሰቦች የተሻገረ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ያነሱት አምባሳደር ነቢል ስለተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች፣ ህወሓት የለውጡ አካል እንዲሆን ጥረት እንደተደረገ ሆኖም ጥረቱን ባለመቀበል ሰሜን እዝን እንዳጠቃ ገልጸዋል፡፡
የአፋር እና አማራ ክልል አካባቢዎችን በመውረር ንጹሃንን እንደገደለ፣ ብዙዎችን እንዳፈናቀለ እና መሰረተ ልማቶችን እንዳወደመም ነው የገለጹት፡፡
ስለ አሜሪካ ህዝብ ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) የእርዳታ መጋዘኖች እና ተሽከርካሪዎች መዘረፍ፤ ስለ ግድቡ የሶስትዮሽ የድርድር ሂደቶች አንስተውም ተወያይተዋል እንደ ኤምባሲው ገለጻ፡፡
ኢትዮጵያ ለሃገራቸው ላደረገችው ድጋፍ ያመሰገኑት የደቡብ ሱዳን የሃገር ግዛት ሚኒስትር ፖል ማዮም አኬች በበኩላቸው የሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት በጠንካራ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴቶች ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል፡፡
በጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የተያዙ አካታች የለውጥ እርምጃዎችን ያወደሱም ሲሆን “ህወሓት በስልጣን ላይ እያለ ተራማጅ መስሎ ቢታይም ጎጠኛ እና ተገንጣይ መሆኑን ማረጋገጡ ያሳዝናል”ም ነው ሚኒስትሩ ያሉት።
የትግራይ ጉዳይ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ቡድኑን ሊጠቀሙ የሚፈልጉ “የጀርባ ኃይሎች” የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ያለመረጋጋት ችግር የበለጠ እያባባሱት እንደሆነ በመጠቆምም “በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ተነጋግሮ እልባት መስጠት” እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትሩ “በብሔራዊ ውይይት ስም የአገዛዝ ለውጥ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም፤ ደቡብ ሱዳንም መሬቶቿ ኢትዮጵያን ለመጉዳት እንዲውሉ አትፈቅድም”ም ነው ያሉት፡፡
በግድቡ ጉዳይ የተፋሰሱ ሃገራት ባልተካተቱባቸው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ላይ መተማመን እንደማይቻል እና የተፋሰሱ ሃገራት ውሃውን ለጋራ ልማት ሊጠቀሙ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡