በደቡብ ሱዳን የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንቱ መኖሪያ መከበቡን ተከትሎ የሰላም መደፍረስ ስጋት ተፈጠረ
ፕሬዝደንት ሳልቫኪርና ማቻር ለአምስት አመታት የቆየውን የእርስበርስ ጦርነት ያስቆመውን የሰላም ስምምነት ከፈረሙ በኋላ ደቡብ ሱዳን ሰላም የሰፈናባት ሆና ቆይታለች

ኪር ማቸርን ማባረራቸውን ተከትሎ በታህሳስ 2013 የተቀሰቀሰው የእርስበርስ ጦርነት ቁጥራቸው 400ሺ የሚገመት ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል
በደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንቱ መኖሪያ መከበቡን ተከትሎ የሰላም መደፍረስ ስጋት ተፈጠረ።
የደቡብ ሱዳን የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቻር አጋር የሆነ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ መያዙንና ወደ ማቻር መኖሪያ ቤት ዙሪያ ወታደሮች መሰማራታቸው የእርስበርስ ጦርነቱ እንዲበቃ ያደረገውን የ2018ቱን የሰላም ስምምነት አደጋ ውስጥ ጥሎታል ተብሏል።
ፕሬዝደንት ሳልቫኪርና ማቻር ለአምስት አመታት የቆየውን የእርስበርስ ጦርነት ያስቆመውን የሰላም ስምምነት ከፈረሙ በኋላ ደቡብ ሱዳን ሰላም የሰፈናባት ሆና ቆይታለች። ነገርግን በተቀናቃኝ ጎሳዎች ተደጋጋሚ ግጭቶች ተነስተዋል።
በትናንትናው እለት የማቸር ቤት በተከበበት ወቅት የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሰራዊት ኃላፊ ከምክትላቸው አንዱ የሆኑትን ሌትናንት ጀነራል ገብሬል ዶፕ ላምን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የማቸር ቃል አቀባይ ፖል ማይ ደንግ ማክሰኞ ምሽት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ቃል አቀባዩ የጋራ መከላከያ ቦርድን የሚያከሽፍና በጥቅሉ ስምምነቱ አደጋው ውስጥ የሚጥል ነው ብለዋል።
"በማቸር መኖሪያ አቅራቢያ የተላኩት የደቡብ ሱዳን ወታደሮች ጉዳይ በእጅጉ አሳስቦናል" ያሉት ቃል አቀባዩ ይህ ድርጊት መተማመንን እንደሚሸረሽር ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን ጦር ቃል አባይ ሜጀር ጀነራል ሉል ራዩ ኮንግ ባወጡት መግለጫ በእስሩም ሆነ ማቻርን ከበዋል በተባሉት ወታደሮች ጉዳይ ምንም ማለት እንማይፈልጉ ገልጸዋል።
ኪር ማቸርን ማባረራቸውን ተከትሎ በታህሳስ 2013 የተቀሰቀሰው የእርስበርስ ጦርነት ቁጥራቸው 400ሺ የሚገመት ሰዎች እንዲገደሉና 2.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።