ትራምፕ በኮንግረስ በታሪክ ረጅም ንግግር በማድረግ ክብረወሰን ሰበሩ
የፕሬዝደንት ትራምፕ በኮንግረሱ ያደረጉት ንግግር አንድ ሰአት ከ39 ደቂቃ ከ32 ሰከንዶች ፈጅቷል ተብሏል

ትራምፕ ባደረጉት ንግግር በተቃዋሚዎች ላይ ከፍተኛ ትችት ከረነዘሩ በኋላ በርካታ የዲሞክራቶች ደግሞ የተቃውሞ ድምጽ አሰምተዋል
ፕሬዝደንት ትራምፕ በስቴት ኦፍ ዘዩኒየን ወይም በኮንግረሱ የጋራ ስብሰባ ላይ በታሪክ ረጅም ንግግር በማድረግ በቀድሞው ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ሰብረዋል።
የፕሬዝደንት ትራምፕ ንግግር አንድ ሰአት ከ39 ደቂቃ ከ32 ሰከንዶች መፍጀቱን ዩኤስኤቱዴይ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የአሜሪካ የፕሬዝደንት ፕሮጀክት ያዘጋጀውን መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል።
ክሊንተን በ2000 ያደረጉት የመጨረሻው ንግግር አንድ ሰአት ከ28 ደቂቃ ከ49 ሰከንዶች ነበር የፈጀው።
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ፕሮጀክት ፕሬዝደንቶች በጋራ የኮንግረስ ስብሰባ ላይ የሚያደርጉትን የጊዜ እርዝማኔ መመዝገብ የጀመረው ሊንዶን ቢ.ጆንሰን በ1964 ካደረጉ ወዲህ ነው።
ትራምፕ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው በኮንግረሱ ያደረጓቸው ንግግሮች በአማካኝ የአንድ ሰአት ከ20 ደቂቃ እርዝማኔ ነበራቸው። ፕሬዝደንት ትራምፕ በካናዳና ሜክሲኮ ላይ የጣሉትን ታክስ ጨምሮ ከመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ጀምሮ ሲያደርጓቸው የነበሩትን እርምጃዎች ተገቢነት አንስተዋል። ትራምፕ ባደረጉት ንግግር በተቃዋሚዎች ላይ ከፍተኛ ትችት ከረነዘሩ በኋላ በርካታ የዲሞክራቶች ደግሞ የተቃውሞ ድምጽ አሰምተዋል።
የቴክሳስ ዲሞክራት ተወካይ የሆኑት አል ግሪን በሪፐብሊካኑ አፈጉባኤ ማይክ ጆንስን እንዲወጡ ከመደረጋቸው በፊት ከመቀመጫቸው በመነሳትና በመጮህ "ስልጣን የለህም" ሲሉ ተናግረዋቸዋል።
ግሪን ባለፈው የካቲት ወር ከጋዛው ጦርነት ጋር በተያያዘ ትራምፕ ከስልጣን እንዲታገዱ ሀሳብ እንደሚያቀርቡ ገልጸው ነበር።
ከግሪን በተጨማሪ በርካታ ዲሞክራቶች ተቃውሟቸውን አቅርበዋል።
ሶስት አመታት ያስቆጠረውን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ለማስቆም ጥረት እያደረጉ ያሉት ትራምፕ ከሩሲያ ጋር ንግግር በመጀመራቸው ዩክሬንና አውሮፓውያን የደህንነት ስጋት እንዲገባቸው ምክንያት ሆኗል። ፕሬዝደንት ትራምፕ በቅርቡ ከዩክሬን ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ጋር በኃይትሀውስ መጋጨታቸው በአውሮፓውያን ዘንድ የበለጠ ስጋት በሩሲያ ደግሞ ዘለንስኪ እንኳን "ተዋረደ" የሚል ስሜትን ፈጥሯል።