ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በወርቅ ሜዳሊያ የተመረቀው ደቡብ ሱዳናዊው ስደተኛ
ደቡብ ሱዳናዊው ድዋል “ኢትዮጵያ ውስጥ በመማሪ እጅግ ደስተኛ ነኝ ለዚህም ኢትዮጵያውያንን አመሰግናለሁ” ብለዋል
ድዋል ዲንግ፤ ኢትዮጵያውን ከደቡብ ሱዳን በመማር ችግሮቻቸውን ሊፈቱ ይገባል ሲልም መክሯል
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ17 ሀገራት የመጡ አንድ ሚልዮን ገደማ የሚሆኑ ስደተኞች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸውን ስደተኞች ከመንከባከብ በዘለለ የትምህርት እድል አግኝተው መጻኢ ህይታቸውን ብሩህ ለማድረግ ይችሉ ዘንድ በተለያዩ ደረጃዎች አስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የትምህርት እድል የሚያገኙበት እድልም ታመቻቻለች።
ደቡብ ሱዳናዊው ድዋል ዲንግ የዚህ እድል ተጠቃሚ ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲ የትምህርት እድል አግኝቶ የወርቅ ሜዳሊያ እስከመሸለም የደረሰ ስደተኛ ነው።
እንደፈረንጆቹ ታህሳስ 2013 በሀገሩ ደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት በመሸሽ በ2014 ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ድዋል፤ በኢትዮጵያ መንግስት፣የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ እና የጀርመኑ አልበርት አይንስታይን አካዳሚክ ሪፉዩጂ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የመግባት እድል ማግኘቱን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግሯል።
ድዋል፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው በሩራል ዴቬሎፕመንት ኤንድ አግሪካልቸራል ኤክስቴንሽን የትምህርት ዘርፍ ያጠና በመጨረሻም በከፍተኛ መዓርግ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆን ለርካታ ስደተኞች አርአያ መሆን የቻለ ወጣት ነው።
ድዋል ዲንግ “ኢትዮጵያ ውስጥ በመማሬ እጅግ ደስተኛ ነኝ፤ ለማህበረሰቤ እና ለሀገሬ የሚጠቅም በቂ እውቀት አግኝቻለሁ፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታ እውቀት እንድገበይ ላስቻሉኝ መምህራን እና ለመላው ኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያገኘው እውቀት በመጠቀም በደቡብ ሱዳን የልማት አጀንዳዎች ላይ የራሱን አሻራ ለማኖር ትልቅ ህልም እንዳለውም ገልጿል ድዋል።
የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው ድዋል ዲንግ፤ ለሀገሩ ደቡብ ሱዳን አደርገግላታለሁ የሚለው ታላቅ ህልም ቢኖረም በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ አሁንም ድረስ እጅጉ እንደሚያሳስበው ግን አልሸሸገም።
“የሀገሬ ጉዳይ አሁንም ያስጨንቀኛል፤ አሁንም ቢሆን የሀገሬ ሰዎች ሰላም እንዲመጣ የሚቻለቸውን እንደሚያደረጉ ተስፋ አድርጋለሁ”ሲልም ያለውን ተስፋ ገልጿል።
ደቡብ ሱዳናዊው ስደተኛ ድዋል ዲንግ ለኢትዮጵያውያን ምክር አለኝ ብለዋል።
“እኔ ከሀገሬ የተሰደድኩት በጦርነት ምክንያት ነው፤ ስለዚህም እናንተ ኢትዮጵያውያን ያላችሁን ችግር ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ወደ ሰላምና ልማት የሚወስዳችሁን መፍትሄ እንድታበጁ እለምናቸዋለሁ” ሲል ጠይቋል።
ሶሞኑን በአዲስ አበባ በሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ የጀርመን መንግስት በዓለም ላይ ለሚገኙ ስደተኞች የትምህርት እድል መስጠት የጀመረበትን 30ኛ ዓመት አክብሯል።
ኤምባሲው ባዘጋጀው መድረክ በኢትዮጵያ የጀርመን አማባሳደር ስቴፋን አወር ጨምሮ በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ እና በኢትዮጵያ የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ ማማዱ ዲያን (ዶ/ር) ተገኝቷል።
አማባሳደር ስቴፋን አወር የጀርመን መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ለስደተኞች የሚሰጠውን የትምህርት እድል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ መንግስት ከጀርመን ጋር በመተባበር ስደተኞች የትምህርት እድል የሚያገኙበት እድል ሲያመቻች መቆየቱን አንስተው እስካሁን 6 ሺህ 600 ስደተኞች የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘታቸው ገልጸዋል።
ከዚህም ውስጥ 4 ሺህ 500 የሚሆኑት ስደተኞች በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ እንዲሁም ቀሪዎቹ 2 ሺህ 100 ስደተኞች በዋናነት በጀርመን መንግስትና ድጋፍ የትምህርት እድል ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ጀርመን በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የትምህርት እድል መስጠት ከጀመረች ሁለት አስርተ ዓመታት ተቆጥረዋል።