ደቡብ ሱዳን በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት የተመድ የአባልነት ክፍያዋን መክፈል አለመቻሏን ገለጸች
ጁባ ለአፍሪካ ሕብረት መክፈል የነበረባትን ክፍያ ባለመክፈል ታግዳ እንደነበርም ይታወሳል
ደቡብ ሱዳንና ሌሎች 5 ሀገራት የአባልነት ክፍያ ባለመክፈላቸው ድምጽ እንዳይሰጡ የተባበሩት መንግስታት ወስኗል
የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት በተጣለባቸው ማዕቀብ ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአባልነት ክፍያቸውን መክፈል እንዳልቻሉ አስታወቁ፡፡
በሀገሪቱ በነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ማዕቀብ ተጥሎባቸው የነበሩት ባለሥልጣናቱ ፣ አሁን ላይ የተባበሩት መንግስታትን የአባልነት ክፍያ መክፈል አልቻልንም ብለዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴንግ ዳኦ ማሊክ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሀገራቸው ባለፈው ታህሳስ ወርር የተጠየቀውን 22ሺ ዶላር ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የላከች ቢሆንም በተጣሉት ማዕቀቦች ምክንያት ገንዘቡ ተመልሷል ብለዋል፡፡
ምክትል ሚኒስትሩ ጁባ ያዘገየችውን ክፍያ ለኒውዮርኩ ተቋም ብትልክም በተጣለባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ምክንያት ገንዘቡ ወደ ሀገሪቱ እንዲመለስ ሆኗል ነው ያሉት፡፡
በአውሮፓውያኑ 2015 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ም/ቤት ሀገሪቱ ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ባደረገችው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ነበር በደቡብ ሱዳን ላይ ማዕቀብ የጣለባት፡፡
በአውሮፓውያኑ 2018 የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ባለመከበሩ ደግሞ ጁባ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ተጥሎባት ነበር፡፡ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባለፈው ሳምንት ደቡብ ሱዳን እና ሌሎች አምስት ሀገራት ከ 2019 ጀምሮ የአባልነት ክፍያ ባለመክፈላቸው ድምጽ እንዳይሰጡ ለጠቅላላ ጉባኤው ፕሬዝዳንት መመሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ደንብ መሠረት በድርጅቱ ውስጥ ለሁለት ዓመት ያህል የአባልነት ክፍያ ያልከፈሉ ሀገራት በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ድምጽ እንዲሰጡ አይፈቀድላቸውም፡፡
ደቡብ ሱዳን ለአፍሪካ ሕብረት መክፈል ያለባትን ዓመታዊ መዋጮ አለመክፈሏን ተከትሎ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው አህጉራዊው ተቋም ሀገሪቱን ከሕብረቱ አባልነት አግዷት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በኋላ ላይም ለአፍሪካ ህብረትመክፈል የነበረባትን የ9 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ መዋጮ ከፍላ ወደ አዲስ አበባው ተቋም መመለሷ ይታወሳል፡፡