ደቡብ ሱዳን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም 334 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አገኘች
የገንዘብ ድጋፉ በኮሮና ቫይረስ እና በእርስ በርስ ጦርነት የተጎዳውን ኢኮኖሚ ይደጉማል ተብሏል
ደቡብ ሱዳን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ላይ ትገኛለች
ደቡብ ሱዳን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) የ334 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አገኘች።
አይ.ኤም.ኤፍ ለደቡብ ሱዳን የገንዘብ ድጋፍ የሰጠው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በተቀዛቀዘው የዓለም ነዳጅ ንግድ የተጎዱ ነዳጅ ላኪ ሀገራት ፈጣን የብድር ድጋፍ ከአንድ ዓመት በፊት ለመስጠት በገባው ቃል መሰረት ነው።
ከዚያ ባለፈም የ334 ሚሊየን ዶላር ድጋፉ የደቡብ ሱዳንን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በማሰብ መሆኑን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን አፍሪካ ዘግቧል።
የደቡብ ሱዳን ባንክ ገዥ ቶንግ ንጎር እንዳሉት የገንዘብ ድጋፉ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመፍታት ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ያግዛል ብለዋል።
ይህ የገንዘብ ድጋፍ ደቡብ ሱዳን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ባለችበት ወቅት መሆኑም ከኮሮና ቫይረስ ጉዳይ በቀላሉ ለማገገም እንደሚረዳም ገዢው ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን ኢኮኖሚ እያንሰራራ ባለው የዓለም ነዳጅ ገበያ ተጠቃሚ ለመሆን ቀስ በቀስ ወደ ውጭ አገራት የሚላከውን የነዳጅ ምርት ለማሳደግ እቅድ እንዳላትም ተገልጿል።
የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለማሳደግ ወደ ውጭ አገራት የሚላከው የነዳጅ ምርትን ለመጨመር አይኤምኤፍ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያደርግም የአገሪቱ ባንክ ገዢ ተናግረዋል።