ሱዳን ከጎረቤቷ የደቡብ ሱዳን ነዳጅ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ጥላው የነበረውን እገዳ አነሳች
ደቡብ ሱዳን በየቀኑ 150ሺ በርሜል ያልተጣራ ወይም ድፍድፍ ነዳጅ በሱዳን በኩል ወደ ውጭ ትልካለች
ሱዳን ባለፈው አመት መጋቢት ወር እገዳውን የጣለችው ነዳጅ ከደቡብ ሱዳን በሱዳን በኩል ወደ ውጭ የሚያስተላልፈው መስመር እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ነው
ሱዳን ከጎረቤቷ የደቡብ ሱዳን ነዳጅ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ጥላው የነበረውን እገዳ አነሳች።
ሱዳን ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን ያልተጣራ ነዳጅ ወደ ቀይባህር ወደብ እንዳይጓጓዝ ለአንድ አመት ጥላው የነበረውን እገዳ የጸጥታ ሁኔታዎች መሻሻላቸውን ተከትሎ ማንሳቷን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሱዳን ባለፈው አመት መጋቢት ወር እገዳውን የጣለችው ነዳጅ ከደቡብ ሱዳን በሱዳን በኩል ወደ ውጭ የሚያስተላልፈው መስመር እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ነው። በወቅቱ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ መጎዳት የሱዳን ጦር እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እያደረጉ ካሉት ግጭት ጋር እንደሚያያዝ ተገልጾ ነበር።
የሱዳን የኢነርጂ እና ፔትሮሊየም ሚኒስቴር ከሁለት ቀናት በፊት ለደቡብ ሱዳን ኢነርጂ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ ካርቱም ከጁባ፣ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩን ከሚቆጣጠረው የሱዳኑ ኩባንያ ባፕኮ ጋር ደህንነቱ የተጠበቀ የነዳጅ ፍስት እንዲኖር ስምምነት በመደረሱ እገዳውን ማንሳቱን ገልጿል።
"ክልከላውን ማንሳታችንን እናሳውቃለን" ሲሉ የሱዳን ኢነርጂ እና ፔትሮሊየም ሚኒስትር ሞሂዲን ናይም ሞሀመድ ለደቡብ ሱዳኑ የፔትሮሊየም ሚኒስትር ፖት ካንግ ቾል ጽፈዋል።
ሮይተርስ ደብዳቤ ትክክለኛ መሆኑን የሱዳን ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለስልጣን እንዳረጋገጡለት ጠቅሷል።
የቻይናውን ሲኤንፒሲ፣ ሲኖፔክን እንዲሁም የማሌዥያውን ፔትሮናስ ጨምሮ በርካታ ኩባንያዎች በግንባታው የተሳተፉበት 1500 ኪሎሜትር የሚረዝመው የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ ከደቡብ ሱዳን የላይኛው አባይ ተፋሰስ እስከ ቀይ ባህር ጫፍ ጠረፍ ፖርት ሱዳን ድረስ የተዘረጋ ነው።
ከደቡብ ሱዳን ዩኒቲ ግዛት እስከ ፖርት ሱዳን የተዘረጋም ሌላ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመርም አለ።
ደቡብ ሱዳን በየቀኑ 150ሺ በርሜል ያልተጣራ ወይም ድፍድፍ ነዳጅ በሱዳን በኩል ወደ ውጭ ትልካለች። ደቡብ ሱዳን ከረጅም ጊዜ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ በ2011 ነበር ነጻነቷን ያወጀችው።
በሱዳን ከሁለት አመት በፊት የተቀሰቀሰው የእርስበርስ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።