በጋምቤላ ክልል በደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች የሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለምን ማስቆም አልተቻለም?
በክልሉ በሚፈጸሙ ድንበር ዘለል ጥቃቶች የሰዎች ህይወት መጥፋትን ጨምሮ ዝርፍያ እና የንብረት ውድመት እንደሚፈጸም ይታወቃል
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለችግሩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት ከደቡብ ሱዳን ሃላፊዎች ጋር እየተነጋገረ ነው ተብሏል
በጋምቤላ ክልል በደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች የሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለምን ማስቆም አልተቻለም?
በጋምቤላ ክልል መነሻቸውን ከደቡብ ሱዳን ያደረጉ ታጣቂዎች የሚፈጽሙት ጥቃት ባለፉት ሶስት እና ከዛ በላይ አመታት በተደጋጋሚ እንደሚከሰት ይታወቃል፡፡
በ2016 መጋቢት ወር የተከሰቱ ሁለት ጥቃቶችን ለአብነት ብናነሳ በአኙዋ ብሔረሰብ ዞን ጆር ወረዳ ውስጥ መጋቢት 26/2016 ዓ.ም ከደቡብ ሱዳን የመጡ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 738 ቤቶች መቃጠላቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ በጥቃቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 14 ሰዎች መቁሰላቸውን እንዲሁም በጆር ወረዳ ከተለያዩ ቀበሌዎች 6100 ሰዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ እና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በመቶዎች የሚቆጠሩ የቁም እንስሳትም በእነዚሁ ታጣቂዎች ተወስደዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ በተከሰቱት የሠላም እጦት ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ 14 የክልሉ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ መንግስት በወቅቱ አስታውቋል፡፡
የክልሉ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኡጅሉ ጊሎ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ ውስጥ በተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጽማሉ።
ሙርሌ የሚባለው ጎሳ በተደጋጋሚ ከብቶችን መዝረፍ እና ህጻናትን አፍኖ መወስድ ላይ ያተኮሩ ጥቃቶችን እንደሚፈጽሙ በነዚህ ጥቃቶችም የሰዎች ህይወት እንደሚያልፍ ሃላፊው አልሸሸጉም፡፡
ለዚህ ደግሞ የደቡብ ሱዳን ሰላም እና ጸጥታ በሀገር ደረጃ በተገቢው መንገድ ያለመጠናከር በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ታጣቂዎች እንዲፈጠሩ ማድረጉን ነው አቶ ኡጂሉ የሚያነሱት፡፡
ኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ፣በጋምቤላ እና በቤንሻንጉል በሶስት ክልሎች ከደቡብ ሱዳን ጋር እንደምትዋሰን የተናገሩት ሃላፊው ሀገራቱ የሚጋሩት ድንበር ሰፊ በመሆኑ አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ በጸጥታ ሀይል ለማስጠበቅ አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኡጅሉ እንዳሉት ታጣቂዎቹ ድንበር ጥሰው የሚገቡባቸው ቦታዎች ቢለዩም በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ሰራዊት በሁሉም ቦታዎች ማሰማራት እና የሚያደርሱትን ጥቃት ማስቆም አልተቻለም።
ኃላፊው “በአንዳንድ ስፍራዎች መከላከያን ጨምሮ የክልሉ የጸጥታ ሀይሎች የድንበር ጥበቃ ያደርጋሉ፤ ነገር ግን በክልሉ በርካታ የደቡብ ሱዳን ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች እንዲሁም በጫካ ውስጥ ድንበር ጥሰው በመግባት ጥቃቶችን ስለሚፈጸሙ በቶሎ ምላሽ ለመስጠት አልተቻለም። ከዚህ ባለፈ አሁን ሀገሪቱ ከምትገኝበት ሁኔታ አንጻር በሁሉም ስፍራዎች ላይ ሰራዊት ማቆም አይቻልም” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ጆር እና አኮቦ በተባሉ የክልሉ ወረዳዎች የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ እንዲሁም ቦታው ረግረጋማ በመሆኑ ለጥቃቶቹ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ እንቅፋት መሆኑን ነው ሀላፊው የሚናገሩት፡፡
“በደቡብ ሱዳን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ መንግስት ታጣቂዎችን መቆጣጠር የሚችልበት አቅም ላይ ባለመሆኑ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ጥቃት የሚያደርሱ ታጣቂዎችን ለመከላከል ስምምነት ተደርሷል” ብለዋል፡፡
በስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት የድንበር ደህንነታቸው በጋራ ለማስጠበቅ የተስማሙ ሲሆን ከዚህ ባለፈም ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር በኩል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎቸ መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡
በዘንድሮው አመት የአደጋ ስጋት ተብለው በተለዩ ስፍራዎች ያሉ የመሰረተ ልማት ችግሮችን የፌደራል መንግስት እና ክልሉ በጋራ ለመቅረፍ ትኩረት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
የመንገድ ልማቶቹ በጆር እና አኮቦ ወረዳዎች የሚሰሩ ሲሆን ድንበር ዘለል ጥቃቶች በሚፈጸሙ ጊዜ አስፈላጊውን ምላሽ ለመስጠት የሚያግዙ እንደሆኑ ተነግራል፡፡
ሌላው ከስደተኞች ጋር ተያያዘው ጉዳይ ሲሆን ክልሉ በኢትዮጵያ በርካታ የውጭ ሀገራት ስደተኞች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
አቶ ኡጅሉ ስደተኞች በአንድ አካባቢ ጸንተው አለመቀመጣቸው ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሆኖብናል ብለዋል።
“የአንዳንድ ስደተኞች በአንድ አካባቢ ጸንቶ አለመቀመጥ ትክክለኛውን የስደተኛ ቁጥር ለመመዝገብ እና ለመቆጣጠር አደጋች አድርጎብናል፤ በአዲሱ አስተዳደር ግን ስደተኞች ድጋሚ እንዲመዘገቡ እና የዲጂታል መታወቂያ እንዲሰራላቸው ከዛም አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ ፤ ለክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ ችግር የማይሆኑበትን መፍትሄ ለማበጀት እየሰራን ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ቀደም ባለው ጊዜ በክልሉ በሚኖሩ ሁለት ጎሳዎች መካከል በኑዌር እና የአኙዋክ መካከል ከዚህ ቀደም ተዳጋጋሚ ግጭት እና የሰላም መደፍረስ የደርስ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሁለቱን ጎሳዎች በማወያየት የክልሉ አዲስ አስተዳደር ዘላቂ ሰላም ማስፈን እንቅስቃሴ መጀመሩን ሰምተናል
ቀደም ብሎ በወሰን ማስከበር፣ በግጦሽ መሬት እና በሌሎች ምክንያቶች በተፈጠሩ ግጭቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም የእርዳታ ድርጅቶች የፌደራል መንግስት እና የክልሉ አስተዳደር በጋራ በመሆን እየሰሩ ነው ተብሏል፡፡