በደቡብ ምስራቅ እስያ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ሰዎች ከአሜሪካ ይልቅ ቻይናን ይመርጣሉ- ጥናት
ቻይና በቀጠናው ያላት ተጽእኖ ፈጣሪነት እያደገ መምጣቱን ጥናቱ ፍንጭ ሰጥቷል
አምና በተመሳሳይ ወቅት በተደረገ ጥናት አብዛኛዎቹ ሰዎች ከቻይና ይልቅ አሜሪካን መርጠው ነበር
በደቡብ ምስራቅ እስያ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ሰዎች ለመምረጥ አስገዳጅ ሁኔታ ከተፈጠረ ከአሜሪካ ይልቅ ቻይናን እንደሚመርጡ ጥናት አመላከተ።
በደቡብ ምስራቅ እሲያ የሚኖሩ ሰዎች ሰዎች መካከል ከግማሽ በላዩ ቻይናን መምረጣቸው ያመላከተው ጥናቱ፤ ይህም ቻይና በቀጠናው ያላት ተጽእኖ ፈጣሪነት እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብሏል።
በደቡብ ምስራቅ እሲያ ውስጥ በሚገኙ ሀገራት በተሰራ የዳሰሳ ጥናት ላይ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል 50.5 በመቶው ቻይና ቀዳሚ ምርጫቸው እንደሆነች የገለጹ ሲሆን፤ ይህ አሃዝ አምና ከተሰራው ጥናት ጋር ሲነጻጸር በ11 በመቶ እድገት አሳይቷል።
በሲንጋፖር በሚገኘው አይ.ኤስ.ኤ.ኤስ-ዩስፍ ኢሻክ ተቋም በየዓመቱ የሚካሄደው የዳሰሳ ጥናት የቅርብ ጊዜ እትም ላይ ቻይና ከአሜሪካ የበለጠ ተመራጭ ስትሆን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ባሳለፍነው ዓመት ማለትም በፈረንጆቹ 2023 አብዛኘዎቹ የደቡብ ምስራቅ እሲያ ሀገራት ነዋሪዎች ከቻይና ይልቅ አሜሪካን መርጠው ነበር ተብሏል።
በአምናው የጥናት ውጤት መሰረትም 38.9 በመቶው ቻይናን የመረጡ ሲሆን፤ 61.1 በመቶው ደግሞ አሜሪካን ምርጫቸው አድርገው ነበር ብሏል ጥናቱ።
በተጨማሪም ቻይና በቀጠናው በኢኮኖሚው ዝርፍም ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገር ተብላ የተመረጠች ሲሆን፤ በጥናቱ ላይ ከተሳተፉ ሰዎች መካከልም 59.9 በመቶው ቻይናን የኢኮኖሚ ተጽእኖ ፈጣሪ ነች ብለዋል።
ነገር ግን 67.5 በመቶ የጥና ተሳታዎች የቻይና ኢኮኖሚ ተጽእኖ ፈጣሪነት ስጋት እንዳሳደረባቸው የተገለጹ ሲሆን፤ ስጋቱ በቬትናም እና በሚያንማር ከፍተኛ ሆኖ ታይቷል።
በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል ከግመሽ በላይ የሚሆኑት ቻይና ያላትን የኢኮኖሚ እና የወታራዊ ኃይል ተጠቅማ በአካባቢው ያሉ ሀገራትን ልታስገድድ ትችላለች ሲሉ ስጋታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ 45.5 በመቶ ተሳታፊዎች ደግሞ ቻይናን እንደማያምኑ ነው የገለጹት።
የኢንዶ-ፓሲፊክ ፕሮግራም ማኔጂንግ ዳይሬክተር ቦኒ ግላዘር የጥናቱ ውጤት የደቡብ ምስራቅ እሲያ ቀጠና ከቻይና ጋር ያለውን የተወሳሰበ ግንኙነት ያሳያል ብለዋል።