የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት በፈቃዳቸው ከሀላፊነት ለቀቁ
አሰልጣኙ ላለፉት ስምንት አመታት በ102 ጨዋታዎች ላይ ብሔራዊ ቡድኑን መርተዋል
በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሳ የነበረችው እንግሊዝ ያለዋንጫ ተሸኝታለች
የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት በገዘ ፈቃዳቸው ከሃለፊነታቸው ለቀዋል፡፡
ባለፉት ስምንት አመታት ብሔራዊ ቡድኑን የመሩት አሰልጣኙ በአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ በስፔን 2ለ1 ከተሸነፉ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው ከሀላፊነታቻው መልቀቃቸውን ያስታወቁት፡፡
በአውሮፓ ዋንጫ ለሁለት ተከታታይ ጊዜ ለዋንጫ ደርሳ የተሸነፈችው እንግሊዝ ዛሬም ለ60 አመታት የቆየ የዋንጫ ርሀቧን ማስታገስ አልቻለችም፡፡
በዚህ አመት ከቡድኑ ጋር ያላቸው ኮንትራት የሚያጠናቅቁት የ53 አመቱ አሰልጣኝ ቀጣይ እጣፈንታቸው ምን እንደሚሆን ሲያነጋግር የቆየ ሲሆን፤ በተለይ በ2026ቱ የአለም ዋንጫ ቡድኑ የሚኖረው ተፎካካሪነት ውጤት ከራቃቸው አሰልጣኝ ጋር ተያይዞ መወያያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
ሳውዝጌት “እንደ ኩሩ እንግሊዛዊ ሀገሬን ወክየ በመጫወቴ እና ብሄራዊ ቡድኑን በመምራቴ ከፍተኛ ክብር ይሰማኛል። ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን የቻልኩትን ሁሉ አድርጊያለሁ አሁን ጊዜው የአዲስ ምዕራፍ መጀመርያ ነው” ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ እግርኳስ ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ቡሊንገሃም አሰልጣኙን የሚተካ ሰው ለመሾም ሂደቶች መጀመራቸውን ገልጸው በቅርቡ የሳውዝጌትን ተተኪ ይፋ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡
አክለውም እንግሊዝ መስከረም 7 በኔሽንሽ ሊግ ከአየርላንድ ጋር በሚኖራት ጨዋታ ከአዲስ አሰልጣኝ ጋር ለውድድሩ እንደምትቀርብ አስታውቀዋል፡፡
ጋሬዝ ሳውዝጌት ላለፉት ስምንት አመታት በ102 ጨዋታዎች ብሔራዊ ቡድኑን መምራት የቻሉ ሲሆን በአራት ትልልቅ ውድድሮች ላይ ቡድኑን ይዘው ቀርበዋል፡፡
ባሰልጣኙ ዘመን ቡድኑ ካደረጋቸው 102 ጨዋታዎች 61 ጊዜ ሲያሸንፍ፣ በ17 ጨዋታዎችን ተሸንፎ በ24ቱ አቻ ወጥቷል፡፡
ቡድኑ በ2018 የአለም ዋንጫ ለግማሽ ፍጻሜ ፣ በ2022ቱ የአለም ዋንጫ ለሩብ ፍጻሜ እንዲሁም በሁለት የአውሮፓ ዋንጫዎች ለፍጻሜ እንዲበቃ አስችለውታል፡፡
አሰልጣኙ በ2016 ቡድኑን ከመረከባቸው ቀደም ብሎ ከ1966 በፊት በ25 ውድድሮች እንግሊዝ 7 የጥሎ ማለፍ ውድድሮችን ማሸነፍ ስትችል በሳውዝጌት አሰልጣኝነት ዘመን ደግሞ 9 የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን አሸንፋለች፡፡
አቅም ያላቸው ተጫዋቾች ቢኖሩትም ጥሩ ቡድን መገንባት አልቻሉም በሚል የተተቹት አሰልጣኙ በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ከስሎቫኒያ ጋር ዜሮ ለዜሮ መለያየታቸውን ተከትሎ ደጋፊዎች የላስቲክ ኮዳዎችን በአሰልጣኙ ላይ በመወርወር ተቋውሟቸውን ሲገልጹ ታይተዋል፡፡
ሳውዝጌት በተጫዋችነት ዘመናቸው ከ1995 እስከ 2004፣ 57 የተለያዩ ዋንጫዎችን ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ማንሳት ችለዋል፡፡
ከ2006 እስከ 2009 ድግሞ ሚድስቦሮን በማሰልጠን ጀምረው በ2013 የእንግሊዝ ከ21 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በማሰልጠን ወደ ዋናው ቡድን ተሸጋግረዋል፡፡