ተጠባባቂ ኃይሎቹ ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ተብሏል
አሜሪካ የሱዳን ተጠቀባባቂ ኃይል ተብሎ በሚጠራው የፖሊስ ኃይል ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታወቀች።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ በድረ-ገጽ ላይ እንዳመላከተው ከሆነ፤ ተጠባባቂው የፖሊስ ኃይሉ በማዕቀቡ ዝርዝር ውስጥ ሊካተት የቻለው በሱዳን የተፈጠረውን አመጽ ተከትሎ “በወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ እና በፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነው” ብሏል
የሱዳን ተጠባባቂ ኃይል አስተዳደራዊ በሆነ መልኩ ከሱዳን ፖሊስ ጋር የተቆራኘ፣ በቀድሞው አገዛዝ የተቋቋመ እና በቅርቡ በሱዳን የተካሄደውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለመጋፈጥ የሚያገለግል ተዋጊ ኃይል መሆኑ ይታወቃል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ወታደራዊ አገዛዝ ያብቃ በሚል ወደ አደባባዮች መውጣት ከጀመሩ ወራትን አስቆጥረዋል።
በዚህም በርካታ በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች ሲሳተፉ የነበሩ ተቃዋሚዎች ከሀገሪቱ ጸጥታ ኃይሎች በተተኮሱ ጥይቶች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወቃል።
በተጨማሪም በሱዳን ያለው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ወደ 400 በመቶ ማሻቀቡ ሱዳናውያን በኑሮ ውድነት እየተፈተኑ እንደሆነ ማሳያ ነው።
በቅርቡ እንኳን በሀገሪቱ የዳቦ ዋጋ በመናሩ የተቆጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ወደ አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ማሳማታቸው የሚታወስ ነው።
ይህም ባለፈው ወርሃ ጥቅምት በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ (ዶ/ር) ይመራ በነበረው መንግስት ላይ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ስልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግስት ላይ ተጨማሪ ጫናን የሚፈጥር ህዝባዊ ቁጣ ነው ተብሎለታል።
ከዳቦ ዋጋ በተጨማሪም የነዳጅ ዋጋ በ50 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም በጀነራል አልቡርሃን ለሚመራው ወታደራዊ መንግስት ሌላኛው ፈተና መሆኑ እየተነገረ ነው።