ካይሮ በደረሱ ጊዜም ወዳጃቸው ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ተቀብለዋቸዋል
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ግብጽን በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡
ቡርሃን የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትራቸውን ሌ/ጄ አህመድ ኢብራሂም ሙፋደልን ይዘው ነው ዛሬ በይፋዊ ጉብኝት ወደ ግብጽ ያቀኑት፡፡
ካይሮ በደረሱ ጊዜም የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተቀብለዋቸዋል፡፡ በአል ኢቲሃዲያ ብሔራዊ ቤተ መንግስትም አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ቡርሃን በካይሮ በሚኖራቸው ቆይታ በሁለትዮሽና በሌሎች የግንኙነት ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
በቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ይመራ የነበረውን የሽግግር መንግስት ፈንግሎ በራሱ ጄነራሎች የሚመራ አዲስ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ማቋቋሙን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
እርምጃውን አጥብቀው የተቃወሙ ሱዳናውያንም ወደየአደባባዩ በመውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ከ6 የበለጡ ወራትን አስቆጥሯል፡፡
ይህም ተቃውሞውን ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን የሚወስደውን ጦሩንና ቡርሃን ሌሎቹንም ባለስልጣናት አስጨንቋል፡፡
ስለሆነም በዚህ እና በሌሎች የጸጥታና ደህንነት፣ የጋራ ወታደራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እንደሚመክሩም ነው የሚጠበቀው፡፡
ቡርሃን ሱዳን ከገጠማት የፖለቲካ ቀውስ መውጣት ብምትችልባቸው መንገዶች ዙሪያ ለመምከር በማሰብ ካይሮ መገኘታቸውንም የግብጽ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ቮከር ፔርዝስ ከሱዳን ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር በካይሮ እንደሚገናኙ ትናንት ማክሰኞ አስታውቆ ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ከእነዚሁ የልዑካን ቡድን አባላት ያገኛሉም ነበር ሚኒስቴሩ ያለው፡፡
ቮከር ፔርዝስ ሱዳንን ከቀውሱ ሊያወጣ የሚችል መግባባት እንዲመጣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት ላይ መሆናቸውን ተመድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ሱዳን ተመድ በሱዳን ቀውስ ጉዳይ ሁኔታዎችን "አመቻች እንጂ አስታራቂ“ መሆን የለበትም ስትል እርምጃውን ተቃውማለች፡፡
ይህ ሂደት ከውጭ አካላት ተጽዕኖ ርቆ መፈጸም አለበት የምትለው ግብጽም የራሷን ሚና እንደምትወጣ ደጋግማ ስትገልጽ ሰንብታለች፡፡ ለዚህም ይመስላል ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ መንግስት ጋር የቀረበ ወዳጅነት ያላቸው ቡርሃን ወደ ካይሮ ያቀኑት፡፡
ግብጽ ቡርሃን በወር ውስጥ ከተጓዙባቸው ሃገራት 5ኛዋ ሆናለች፡፡ ከአሁን ቀደም ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ አረብ ኤሚሬትስ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ ተጉዘዋል፡፡
የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ መሃመድ ሃምዳን ዳገሎ በቅርቡ አረብ ኢሚሬትን ጨምሮ በተለያዩ የመካለኛው ምስራቅ ሃገራት ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡