አል-ቡርሃን የተመድ ልዩ መልእክተኛን ከሱዳን ሊያባርሩ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ
ፕሬዝዳንቱ፤ ልዩ መልእክተኛው ቮልከር ፔሬዝ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ነው ብለዋል
ፔሬዝ ሱዳን "ህገ መንግስታዊ መንገዱን የማደስ ካላጠናቀቀች አደጋ ላይ ትወድቃለች የሚል ሪፖርት ማቅረባቸው” በአል-ቡርሃን ጥርስ አስነክሶባቸዋል
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልእክተኛ ከሱዳን ሊያባርሩ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ።
አል-ቡርሃን፤ በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልእክተኛው ቮልከር ፔሬዝ “በሱዳን ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ያቁም” ሲሉም ጠይቀዋል።
የሉዓላዊው ምክር ቤት ፕሬዝዳንቱ አል-ቡርሃን ፤ ቮልከር ፔርዝ ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጭ እያደረጉት ያለው ተግባር ከሀገሪቱ ሊያስባርራቸው የሚችል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት በሱዳናውያን መካከል ውይይቶችን ከማመቻቸት በዘለለ በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ሲሉም አል-ቡርሃን አሳስበዋል።
አል-ቡርሃን አክለውም፤ በሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ላይ እየተደረገ ያለው የስም ማጥፋት ዘመቻ ተገቢነት የለውም ሲሉም ቅሬታቸው ገልጿል።
“የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ስም የማጥፋት ዘመቻ እየደረሰባቸውም ቢሆን በሀገር ጉዳይ ችላ የሚሉት ነገር የለም” ሲሉም ተናግረዋል።
የታጠቁ የመንግስት ሃይሎች መቼም ቢሆን ሀገሪቱን በብቸኝነት የመምራት ፍላጎት ኖሮዋቸው አያውቅም ያሉት አል-ቡርሃን፤ አሁንም ቢሆን የተቃውሞ ኮሚቴዎችንና ብሔራዊ ኃይሎችን ለውይይትና ለሚፈለገው ሀገራዊ መግባባት መጥራታቸው እንዳላቆሙ አንስቷል።
ይህ ባለበት ሁኔታ፤ በሱዳን የሚስተዋለው የተመድ እንቅስቀሴ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚቃረን መሆኑን ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን አስታውቀዋል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ በካርቱም የሚገኘውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ "UNITAMS" ተግባራት ላይ ቁጥጥር መጀመሩን አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።
ሚኒስቴሩ ይህንን ያለው፤በሱዳን የሚገኙት የተመድ ልዩ መልእክተኛ በሱዳን ካሉ ሰልፎችና ተቃውሞዎች ጋር በተያየዘ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በርካታ ውንጀላዎችን የያዘ አጭር መግለጫ ከሰጡ በኋላ ነው።
የፔሬዝ መግለጫ በሀገሪቱ ከሚገኙ የሲቪል እና ወታደራዊ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ተልዕኮው ያካሄደውን የምክክር ውጤት ያካተተ ሲሆን፥ ሱዳን "ህገ መንግስታዊ መንገዱን የማደስ ሂደቱ እስካላጠጠናቀቀች ድረስ ወደ ትጥቅ ግጭት ልትገባ እንደምትችል በስጋት ያስቀመጠ ነበር።