በስፔን በደረሰው የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር 95 ደረሰ
ከሰሞኑ በደረሰ የጎርፍ አደጋ በተመታው የቫሌንሲያ ክልል ተጨማሪ አደጋ ሊከሰት እንደሚችልተነግሯል
በአንዳንድ አካባቢዎች የውሀ መጠኑ ባለመቀነሱ አገልግሎቶችን ለማስጀምርና ሰብአዊ ድጋፎችን ለማዳረስ አደጋች ሆኗል
ከሰሞኑ በስፔን የደረሰውን አስከፊ የጎርፍ አደጋ ተከትሎ የነፍስ አድን ቡድኖች ከጎርፍ አደጋ በኋላ የጠፉ ሰዎችን በማፈላለግ ተጠምደዋል፡፡
የስፔን ባለስልጣናት በሀገሪቱ ከሶስት አስርት መታት ወዲህ አስከፊ ነው በተባለው የጎርፍ አደጋ ምን ያህል ሰዎች የደረሱበት እንዳልታወቀ እስካሁን የገለጹት ነገር የለም፡፡
የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ማርጋሪታ ሮበልስ በበኩላቸው የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተናግረው፤ የነፍስ አድን ሰራተኞች በውሀ በሰጠሙ መኪናዎች እና በመኖርያ መንደሮች አካባቢ የጠፉ ሰዎችን ለመፈለግ የሚያደርጉትን ጥረት መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡
በአደጋው እስካሁን የሟቾች ቁጥር 95 መድረሱ ሲነገር ስፔን በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት በደረሰበት የቫሌንሲያ ክልል ተጨማሪ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በዛሬው እለት ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች፡፡
የሜትሮሎጂ ባለሙያዎች ማክሰኞ እለት በቫሌንሲያ አንዳንድ ክፍሎች ለስምንት ሰአታት የጣለው ዝናብ የአንድ አመት ዝናብ እንደሆነ እየተናገሩ ነው።
በዚህም የመኖርያ መንደሮችን እና የእርሻ መሬቶችን በማጥለቅለቅ የአለም ሁለት ሶስተኛ የብርቱካን ምርት በምታመርተው ሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
ከዚህ ባለፈም የተለያዩ የቁም እንስሳቶችን ጎርፉ ጠራርጎ የወሰደ ሲሆን ፣ በመኖርያ ቤቶች ፣ በመንገድ ፣ በኤሌክትሪክ እና ሌሎች መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተሰምቷል፡፡
በአንዳንድ መንደሮች የውሀው መጠን አሁንም ባለመቀነሱ አገልግሎቶችን ለመጠገን እና ሰብአዊ ድጋፎችን ለማደረስ አዳጋች እንዳደረገው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከባድ ዝናብ ያስከተለው ማዕበል ወደ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ እየተንቀሳቀስ ነው፤ በአካባቢው በተለይም በካስቴሎን ሰሜናዊ ክፍል አሁንም ኃይለኛ አውሎ ነፋስ መኖሩ ተገልጿል።
መጥፎ የአየር ሁኔታው ይቀጥላል ያሉት የስፔን የአደጋ ጊዜ ባለስልጣናት ሰዎች ወደ አካባቢው እንዳይሄዱ በፍጥነት ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲዛወሩ እያስጠነቀቁ ነው፡፡
መንግስት በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ እና ለማቋቋም ቃል ገብቷል፡፡