የስፔን ፖሊስ በአባሉ ቤት ላይ ፍተሸውን ያደረገው 13 ቶን መጠን ያለው አደገኛ እጽ ከኢኳዶር ወደ ስፔን ሲገባ መያዙን ተከትሎ ነበር
ከባድ ወንጀሎችን እንዲከላከል በተሾመው ፖሊስ ቤት 20 ሚሊዮን ዩሮ ተደብቆ ተገኘ፡፡
ኦስካር ሳንቼዝ ጊል የስፔን ፖሊስ መኮንን ሲሆን በሀገሪቱ የሚፈጸሙ ድንበር ዘለል እና አደገኛ ወንጀሎችን እንዲያከላከል ሀላፊነት ተሰጥቶት ነበር፡፡
መነሻውን ከላቲን አሜሪካዋ ኢኳዶር ያደረገው መርከብ ሙዝ ጭኖ ወደ ስፔን እሚገባ መስሎ በውስጥ የጫነው ግን ሲመረመር 13 ቶን የሚመዝን ኮኬይን የተሰኘው አደገኛ እጽ መሆኑን ፖሊስ ይደርስበታል፡፡
ይህን ተከትሎ በተደረገው ምርመራ አደገኛ እጹ ወደ ስፔን በሙዝ ስም እንዲመጣ የተደረገው ከፖሊሶች ጋር በተደረገ ስምምነት መሆኑ ይደረስበታል፡፡
ይህን ተከትሎ በፖሊስ አባሎች ላይ በተደረገ ክትትል ኦስካር ሳንቼዝ ጊል እጁ እንዳለበት ተደርሶበት መኖሪያ ቤቱ እና ቢሮው ላይ ጥብቅ ፍተሸ እንደተደረገ ተገልጿል፡፡
በከባድ ግድያ ወንጀል ሲፈለግ የነበረው ሰው ፖሊስ ሆኖ ተገኘ
የፖሊስ መኮንን በማድሪድ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ግድግዳ ውስጥ 20 ሚሊዮን ዩሮ ደብቆ መገኘቱን ኤልሙንዶ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ኦስካር ሳንቼዝ እና የፖሊስ አባል የሆነችው ፍቅረኛው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በስራ ቦታው ውስጥም አንድ ሚሊዮን ዩሮ ተገኝቷል፡፡
ወደ ስፔን የገባው አደገኛ እጽ ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ለማስገባት ሌሎች ጥረቶች እንደነበሩም ተገልጿል፡፡
የስፔን ፖሊስ ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ እስካሁን 15 ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉንም አስታውቋል፡፡