ቦሪስ ጆንሰን ስልጣን እንዲለቁ እየተጠየቁ ያሉት በዋናነት በራሳቸው ፓርቲ አባላት ነው
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስልጣን እንዲለቁ የሚደረጉ ጫናዎች እየበረቱ ነው ተብሏል፡፡
ጫናዎቹ ከራሳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊዎች ጭምር የሚመጡ ናቸው፡፡
ጆንሰን ስልጣን እንዲለቁ የሚያጠይቁ ወግ አጥባቂ የምክር ቤት አባላት ተበራክተዋል ያለው ስካይ ኒውስ ከዳውኒንግ ስትሪት ቤተ መንግስት የመውጣታቸው ነገር የሚቀር አይመስልም ሲል ዘግቧል፡፡
ተነባቢው የእንግሊዙ ጋዜጣ ዘ ጋርዲያንም የጆንሰን የማይቀር የመሰናበት እጣ ፋንታ እውን እየሆነ መጥቷል ሲል ብሏል፡፡
የቀድሞው ጋዜጠኛ እና የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስልጣን እንዲለቁ ጥያቄዎች መቅረባቸውንም ብዙሃን መገናኛዎቹ ዘግበዋል፡፡
እንግሊዛውያን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ሳለ ጆንሰን በጽህፈት ቤታቸው ደጋግመው የተዝናኖት መርሃ ግብር ማዘጋጀታቸው ከባድ ህዝባዊ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡
ብዙዎች ‘ፓርቲ ጌት’ በሚል ሰይመው “ቅሌት ነው” ካሉት ከዚህ ድርጊት ጋር በተያያዘም ነው ስልጣን እንዲለቁ መጠየቅ የጀመረው፡፡
ከእለት ዕለት እየበረታ በመጣው በዚህ ጥያቄ ምክንያት የጆንሰን ጠቅላይ ሚኒስትርነት በቶሎ ሊያበቃ እንደሚችልም በመነገር ላይ ይገኛል፡፡
የራሳቸው ፓርቲ አባላት ናቸው ጆንሰንን ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ለማሰናበት ጫና እያደረጉ ያሉት፡፡ 20 ገደማ ወግ አጥባቂ የምክር ቤት አባላት ጆንሰን የመተማመኛ ድምጽን አጥተው ጫና ውስጥ እንዶገቡና ስልጣናቸውን እንዲለቁ ሌሎችን እያግባቡ ነው ተብሏል፡፡ ሆኖም ማግባባቱ ከዳር የሚደርሰው በትንሹ 54 የምክር ቤት አባላት ጥያቄውን ሲደግፉ ብቻ ነው፡፡
ቦሪስ ጆንሰንም ስልጣናቸውን “በቀላሉ ላለማጣት” የባለስልጣናት ሹም ሽር እያደረጉ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የምክር ቤቱ የካቢኔ ጉዳዮች ተጠሪን የጽህፈት ቤታቸው ኃላፊ አድርገው መሾማቸውም ነው የተነገረው፡፡ የሎንደን ከንቲባ እያሉ አብሯቸው ይሰራ የነበረን ሰው ቃል አቀባይ አድርገው ሾመዋልም ተብሏል፡፡