ዩናይትድ ኪንግደም ጦሯን ሲያግዙ የነበሩ 3 ሺ ገደማ አፍጋናውያንን በሃገሯ ልታሰፍር ነው
ሆኖም አሁን ጦሩ አፍጋኒስታን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ዩኬ በቶሎ ትወስዳቸዋለች ነው የተባለው
አፍጋናውያኑ በትርጁማንነትና በሌሎችም ስራዎች ጦሩን ሲያግዙ ነበር ተብሏል
ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በአፍጋኒስታን ዘመቻ በትርጉም እና ሌሎች ስራዎች ሲያግዟት የነበሩ 3 ሺ ገደማ አፍጋናውያንን እና ቤተሰቦቻቸውን በሐገሯ ልታሰፍር ነው፡፡
ዩኬ ይህን የምታደርገው ጦሯን ሲያግዙ ለነበሩ አፍጋናውያን በቂ ከለላ አልሰጠችም በሚል በቀድሞ ከፍተኛ የጦር አመራሮቿ መወቀሷን ተከትሎ ነው፡፡
ለወቀሳው ምላሽ የሰጠው የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ ተልዕኮውን ሲያግዙ የነበሩ 500 አፍጋናውያንን ከነቤተሰቦቻቸው በቶሎ ለማዛወር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአፍጋኒስታን ተሰማርቶ የነበረው የአሜሪካ ጦር በቶሎ ሃገሪቱን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በትርጁማንነት እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ሲያገለግሉ በነበሩ አፍጋናውያን ላይ ጫናው በዝቷል፡፡
በታሊባን ጦር ዒላማ ልንደረግ እንችላለን በሚል ብዙዎች ስጋት ላይ ወድቀዋል፡፡
ይህን ተከትሎ አሜሪካን ጨምሮ ወታደሮቻቸውን አሰማርተው የነበሩ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ድርጅት (ኔቶ) አባል ሃገራት ጥቂት የማይባሉ አፍጋናውያንን ከሃገራቸው እያስወጡ ነው፡፡
ለ20 ዓመታት በዘለቀው የአፍጋን ቆይታዋ 1,360 አፍጋናውያንን ወደ ሃገሯ የወሰደችው ዩናይትድ ኪንግደምም ተጨማሪ 3 ሺ ገደማ አፍጋናውያንን በቶሎ ለመውሰድ በመስራት ላይ መሆኗን ገልጻለች፡፡