ኢትዮጵያ የወንዴ የዘር ፍሬ ወይም እንቁላል መለገስ የሚያስችል ህግ የላትም ተባለ
ኢትዮጵያ ወላጆቻቸው በግልጽ የማይታወቁ ልጆች እንዲወለዱ የሚፈቅድ ህግ እንደሌላት ተገልጿል
ልጅ በተፈጥሯዊ መንገድ መውለድ ያልቻሉ ባለትዳሮችን ብቻ በሳይንሳዊ ዘዴ በመርዳት ልጅ እንዲወልዱ የሚያደርግ ህክምና በሀገር ውስጥ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል
ኢትዮጵያ የወንዴ የዘር ፍሬ ወይም እንቁላል መለገስ የሚያስችል ህግ የላትም ተባለ፡፡
ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ወንዶች የዘር ፍሬያቸውን ሴቶች ደግሞ እንቁላላቸውን መለገስ እንደሚቻል የሚያሳይ ዘገባ መሰራቱ ይታወሳል፡፡
ቢቢሲ አማርኛ እንደዘገበው ከሆነ መሰረቱን በትግራይ ክልል መዲና መቀሌ ከተማ ያደረገ አንድ የህክምና ተቋም የወንድ ዘር ፍሬያቸውን ለሚለግሱ 10 ሺህ ብር እንዲሁም እንቁላላቸውን ለሚለግሱ ሴቶች ደግሞ 30 ሺህ ብር እንደሚከፍል አስታውቋል፡፡
ይህ የህክምና ተቋም ልጅ መውለድ ያልቻሉ ሰዎችን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል ህክምና መጀመሩን እና ለዚህም የተለያዩ መስፈርቶችን አስቀምቷል፡፡
ይህን መነሻ በማድረግም አልዐይን አማርኛ የጤና ሚኒስቴርን በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረ ሲሆን ኢትዮጵያ ከበጎ ፈቃደኞች በተለገሱ የዘር ፍሬዎች አልያም እንቁላል ልጅ እንዲወለዱ የሚፈቅድ ህግ እንደሌላት አስታውቋል፡፡
በሚኒስቴሩ የጤና እና ጤና ነክ ተቋማት እና ባለሙያዎች ቁጥጥር ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ እንዳልካቸው ጸዳል ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ መንገድ ልጅ መውለድ ያልቻሉ ባለትዳሮች ወይም ጥንዶች ከራሳቸው ብቻ በተገኘ የዘር ፍሬ ልጅ እንዲወልዱ የሚረዳ ህክምና በሀገር ውስጥ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለ550 ልጆች አባት የሆነው ሆላንዳዊ የዘር ፍሬውን እንዳይለግስ ታገደ
ከዚህ ውጪ ግን “ከበጎ ፈቃደኞች በተሰበሰበ የወንድ የዘር ፍሬ ወይም እንቁላል ልጆች እንዲወለዱ የሚፈቅድ አሰራር በሀገሪቱ የለም የለም” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህን የሚፈቅድ አሰራር ከሌላት በመቀሌ ከተማ የዘር ፍሬ እና እንቁላል ከበጎ ፈቃድ እሰበስባለሁ የሚለው ተቋም እንዴት ህጋዊ ተቋም ሊሆን ቻለ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም ክልሎች ከጤና ጋር የተያያዙ የህክምና ፈቃዶችን የመስጠት ስልጣን አላቸው ነገር ግን የሚሰጡት ፈቃዶች ከሀገሪቱ የጤና ፖሊሲ እና አሰራር ጋር በማይጋጭ መልኩ መሆን አለበት ብለዋል፡፡