የሕዳሴ ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት በዛሬው ቀን አል-ቡርሃን ኢትዮጵያ ገብተዋል
በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፍራዎችን የሚጎበኙ ሲሆን በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚያደርጉት ውይይት ይጠበቃል
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሕዳሴው ግድብ ላይ ኢትዮጵያን ያስቆጣ አስተያየት ከሰጡ በኋላ አል-ቡርሃን ቀድመው ግብፅን ጎብኝተዋል
ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን ለ 2 ቀናት ጉብኝት ኢትዮጵያ ገቡ
ከሰሞኑ በካይሮ ጉብንት አድርገው የነበሩት የሱዳን የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱል ፈታህ አል-ቡርሃን ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ዛሬ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ አል-ቡርሃን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የሱዳን የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበሩ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት በሚኖራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽና በተለያዩ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
የሱዳን የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አል-ቡርሃን እና አቢይ ዛሬ ወደ አዳማ በማቅናት በከተማዋ የሚገኘውን የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሚጎበኙም ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ባለፈ በዱከም የሚገኘውን ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚጎበኙ ሲሆን ጆይ ቴክ ፋርምም እንዲሁ የመጀመሪያ ቀን የጉብኝታቸው አካል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በነገው ዕለት ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሁለተኛ ቀን ጉብኝታቸው ደግሞ እንጦጦ ፣ ዩኒቲ እና ሸገር ፓርኮችን ይጎበኛሉ፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቀው ውይይት የአል-ቡርሃን ጉብኝት ዋነኛው ተጠባቂ ጉዳይ ነው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያ ግድብ ላይ ከሰጡትና ኢትዮጵያውያንን ካስቆጣው አስተያየታቸው በኋላ ፣ አል-ቡርሃን ባለፈው ማክሰኞ ከግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በካይሮ የተወያዩ ሲሆን በዚህ ወቅት ካይሮ እና ካርቱም የሕዳሴ ግድብን ሙሌት እና አሰራሩን አስመልክቶ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የእስራኤል-ሱዳን ስምምነትን ከእስራኤል ጠ/ሚኒስተር ኔታንያሁ ፣ ከሱዳኑ አቻቸው ሃምዶክ እና የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት ሊቀመንበር አብዱ ልፈታህ አል-ቡርሃን ጋር ከሳምንት በፊት በስልክ ባደረጉት ንግግር ወቅት ነበር ትራምፕ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ “ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች” የውሃ ፍላጎቷን ስለሚገታ “አንድ ነገር ማድረግ አለባት” በሚል ጸብ አጫሪ እና ግብጽን ለጦርነት የሚያበረታታ የሚመስል ንግግርም ያደረጉት፡፡ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር በውይይቱ ወቅት የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በሚካሔደው ውይይት እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱን ንግግር በመቃወም የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ ከማውጣትም ባለፈ የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ የሚገኙትን የአሜሪካ አምባሳደር በመጥራት በንግግሩ ዙሪያ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር የተለያዩ የአሜሪካ ሴናተሮችን እና የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ በበርካታ አካላትም ተተችቷል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮች ድርድር ዛሬ ይቀጥላል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ዛሬ እንደሚቀጥል የሱዳን የመስኖ ሚኒስቴር ትናንት አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ በመግለጫ በሀገራቱ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ድርድር እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡