በውይይቱ የሦስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይና የውኃ ሚኒስትሮች ይሳተፋሉ
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትጵያ፣ሱዳንና ግብፅ መካከል ሲደረግ የነበረው ድርድር ዛሬ እንደሚቀጥል የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የዛሬው ውይይት በግድቡ አጠቃላይ ሙሌት እና አመታዊ ክዋኔ ህጎች እና መመሪያዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ (ኢ/ር) የዛሬው ስብሰባ የተጠራው የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር በሆነቸው ደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግንኑነትና ትብብር ሚኒስትር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በውይይቱም የሦስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይና የውኃ ሚኒስትሮች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡
ለአንድ ወር ተቋርጦ የነበረው ይኸው ድርድር ዛሬ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባሳለፍነው ማክሰኞ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ድርድሩ የቆመው በሀገራቱ የውስጥ ጉዳይና ሱዳን የድርድሩ አካሄድ (ሞዳሊቲ) ይቀየር የሚል ጥያቄ በማንሳቷ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ገልጸው ነበር፡፡ ሱዳን ወደ ድርድሩ እንደምትመለስ በቅርቡ መግለጿን ተከትሎ የዛሬው ድርድር ሦስቱንም ሀገራት አሳትፎ ነው የሚካሔደው፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁን ላይ ግንባታው 78 በመቶ መድረሱን ዶ/ር ስለሺ በቀለ (ኢ/ር) በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ ባሳለፍነው ክረምት የመጀመሪያ ደረጃ የውኃ ሙሌት መከናወኑ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ዓመት ክረምት ላይ ደግሞ ሁለተኛው ዙር ሙሌት እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡
ግብጽና ሱዳን ከዚህ ቀደም ግድቡ ጉዳት ያደረስብናል የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ የነበሩ ቢሆንም የመጀመሪያው ዙር ውኃ ሙሌት ከተጠናቀቀ ወዲህ ግን የውኃ መቀነስም ሆነ ሌላ ተያያዥ ጉዳት ስለማጋጠሙ ከካርቱምም ሆነ ከካይሮ የተባለ ነገር የለም፡፡
አንዳንድ የሱዳን ፖለቲከኞችና ምሁራን የሕዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ቢፋጠን ከጎርፍ አደጋ እንድን ነበር የሚሉ አስተያየቶችን መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ፣ ከኢትጵያ ለሱዳን በጎርፍ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ላቀናውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለተመራው ቡድን “ቶሎ ብላችሁ ግድቡን ጨርሱ፤ እኛንም ከጎርፉ ትታደጉናላችሁ” እንዳሏቸው አምባሳደር ዲና ገልጸው ነበር፡፡ ይሁንና በሌላ በኩል ከሕዳሴ ግድብ በታች ባለው የሱዳን ግድብ ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል በሚል ስጋት ፣ አስገዳጅ ስምምነት ሳይደርስ ኢትዮጵያ ግድቡን እንድትሞላ እንደማይፈቅድ የሱዳን መንግሥት በተደጋጋሚ አቋሙን አስታውቋል፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት ላይ የመድረስ ፍላጎት የላትም፡፡