ፕሬዝዳንት ራጃፓክሳ ከስሪላንካ ወጥተዋል ተብሏል
የስሪላንክ ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ ስልጣን ለመልቀቅ ስለመወሰናቸው ተነገረ።
ራጃፓክሳ ስልጣን ለመልቀቅ መወሠናቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክረምሲንግ ማሣወቃቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
የሃገሪቱ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤም ይህንኑ አስታውቀዋል፤ ፕሬዝዳንቱ ከመጪው ረቡዕ ጀምሮ በይፋ ስልጣን እንደሚለቁ በመጠቆም።
ሆኖም ራጃፓክሳ በራሳቸው ለመልቀቅ ስለመወሠናቸው ያሳወቁት ነገር የለም።
ፕሬዝዳንቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስሪላንካውያን በጥብቅ ይጠበቅ ወደነበረው መኖሪያቸው ሰብረው መግባታቸውን ተከትሎ መሸሻቸው ይታወሳል።
ትናንት እሁድ የወጡ መረጃዎችም ራጃፓክሳ ከስሪላንካ መውጣታቸውን አመልክተዋል።
የራጃፓክሳን ስልጣን ለመልቀቅ መወሰን ያሳወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክረምሲንግ ራሳቸው ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት እንደሚቋቋምና ስልጣን እንደሚለቁ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቃቸውን ተከትሎ የሽግግር መንግስት የሚቋቋም ከሆነ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤው ጊዜያዊውን መንግስት ይመራል።
ሆኖም አፈ ጉባኤው የሚመራው ምክር ቤቱ በ30 ቀናት ውስጥ ተተኪ መሪዎችን እስከሚመርጥ ድረስ ብቻ ነው።
ሆኖም የመሪዎቹ መልቀቅ ብቻ በቂ አይደለም ያሉና ወደ ፕሬዝዳንቱ መኖሪያ የገቡና ከበው የተቀመጡ ስሪላንካውያን ተጨማሪ የለውጥ እርምጃዎች እስከሚወሰዱና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንግስት እስከሚመሠረት ድረስ ተቃውሟችን አይቆምም ብለዋል እንደ ሮይተርስ ዘገባ።
በዋናነት ቱሪዝም ላይ የተመሠረተው የስሪላንካ ምጣኔ ሐብት በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወዲህ ከባድ ፈተና ውስጥ ወድቋል።
በፕሬዝዳንት ራጃፓክሳ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎም ፈተናዎቹን ለመፍታት ቀርቶ ለማቅለል ሳይችሉ ስለመቅረታቸውም ይነገራል።
ይህ ከነበረው የብድር ጫናና የነዳጅ እጥረትን ተከትለው ካጋጠሙ የዋጋ ንረት ችግሮች ጋር ሲደማመር ሃገሪቱን ለከፋ ችግር ስለመዳረጉ ነው የሚነገረው።