ቅዱስ ጊዮርስ ጌታነህ ከበደን ጨምሮ 4 የዋናው እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾቹን አገደ
ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለም መስፍን ናቸው ከቡድኑ የታገዱት
ከዚህ ቀደም ቡድኑ በባህርዳር በነበረው ቆይታም የስነ ምግባር ጉድለት ፈጽመው ነበር
የቅዱስ ጊዮርስ ስፖርት ማህበር ጌታነህ ከበደን ጨምሮ አራት የዋናው እግርኳስ ቡድን ተጫዋቾቹን ማገዱን ስታወቀ።
የስፖር ማህበሩ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ በ2013 ዓ.ም በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ቡድኑ ውጤታማ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሶ፤ “ቡድኑ እየተደረገለት ካለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አንጻር የሚጠበቅበትን ያህል አርኪ የሚባል እንቅስቃሴዎችን እያደረገ አይደለም” ብሏል።
“በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፎ አልፎ በቡድኑ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ተጫዋቾቻችን የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪና የስነ-ምግባር ጉድለት እጅጉን የሚያስቆጭ ነው” ሲልም ክለበት አስታውቋል።
ትናንት ቡድኑ በድሬዳዋ ስታዲየም ከጅማ አባጅፋር ጋር ካካሄደው የ20ኛ ሳምንት ጨዋታ በኃላ ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለም መስፍን ከፍተኛ የዲሲፒሊን ግድፈት መፈጸማቸውንም ክለቡ አስታውቋል።
አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከዚህ ቀደም ቡድኑ በባህርዳር በነበረው ቆይታም የስነ ምግባር ጉድለት ፈጽመው የነበረ ቢሆንም አጠቃላይ ለቡድኑ ውጤታማነትና አንድነት ሲባል በማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ተደርጎ እንደነበረም አስታውሷል።
የክለቡ ስራ አመራር ቦርድ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ተጫዋቾቹ በፈጸሟቸው የዲስፕሊን ግድፈቶች ዙሪያ የቡድን መሪው በተፈጸመው የሥነ ምግባር ጉድለት ዙሪያ በዝርዝር በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ቦርዱ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለም መስፍን ለጊዜው ከቡድኑ ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑንም ገልጿል
ስለሆነም አራቱም ተጫዋቾች ከድሬዳዋ በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጉንም የቅዱስ ጊዮርስ ስፖርት ማህበር በመግለጫው አስታውቋል።