ሁለት ጊዜ ለኢትዮጵያ የተዋጉት ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ሃውልት ቆመላቸው
ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ “ወንድሜ በህይወት ላለመኖሩ በቂ ማስረጃ አልቀረበልንም ” ማለታቸው ይታወሳል
ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መታሰቢያ ሃውልት የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ በተገኙነት ተመርቋል
ሁለት ጊዜያት ለኢትዮጵያ የተዋጉት እና በሕይወት መኖር አለመኖራቸው ያልተረጋገጠው ኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስ የመታሰቢያ ሐውልት ቆመላቸው።
በኢትዮጵያ ደቡብ ክልል በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስ የመታሰቢያ ሐውልት መቆሙን አል ዐይን ከዞኑ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የመታሰቢያ ሃውልቱ በዛሬው እለት የደቡብ ክልል ርዕሰ መሰተዳድር ርስቱ ይርዳው፣ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣ የኮሎኔል በዛብህ ቤተሰቦች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ተመርቋል።
በሆሳዕና መሐል ከተማ ላይ የቆመው የኮሎኔሉ ሐውልት 17.5 ሜትር ቁመት ያለው ሲሆን፤ በ5 መቶ 30 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ነው።
ለአጠቃላይ ግንባታው 45.5 ሚሊዮን ወጪ ተደረጎበት በሀዲያ ልማት ማህበር (ሀልማ) የተሰራ መሆኑም ተንገሯል
'ኮሎኔል በዛብህ ለረጅም ጊዜ በፖለቲካ ተሳትፏቸው የሚታወቁት የፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ወንድም ናቸው። ኮሎኔል በዛብህ በዉጊያ ወቅት በኤርትራ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ በህይወት አሉ ወይስ የሉም የሚል ድምዳሜ ላይ እስካሁን አለመደረሱን ቀደም ሲል ቤተሰቦቻቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
በደርግ ዘመነ መንግስት የጦር አውሮፕላን አብራሪ የነበሩት የአንጋፋው ፖለቲከኛ በየነ ጴጥሮስ(ፕ/ር) ታናሽ ወንድም ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ በሕይወት አሉ ወይስ የሉም የሚለው ጉዳይ መነጋገሪያ ከሆነ ቆየት ብሏል። ከሎኔል በዛብህ እየተዋጉ ሳለ በኤርትራ ሕዝብ ነጻነት ግምባር ሰራዊት ተይዘው ኤርትራ መቆየታቸው ይታወሳል።
በ2013 ዓ.ም ለንደን የሚገኘው ኤርትራ ፕሬስ የተሰኘ ድረ-ገጽ ኮሎኔል በዛብህ መሞታቸውን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከሰሙ ቆይተዋል ማለቱን ተከትሎ ጉዳዩ እንደ አዲስ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
የደርግ መንግስት በ1983ዓ.ም ከወደቀ በኋላ ኮሎኔሉ ተይዘው ከነበረበት ኤርትራ ወደ ሀገራቸው ቢመለሱም ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1990ዓ.ም ዳግም ወደ ጦርነት ሲያመሩ በድጋሚ የጦር አውሮፕላን አብራሪ በመሆን ጦርነቱ ላይ ዘምተው ነበር።
አዋጊ የነበሩት ኮሎኔሉ በዚሁ ጦርነት ወቅት ያበሩት የነበረው አውሮፕላን ተከስክሶ ዘለው በጃንጥላ ሲወርዱ ለሁለተኛ ጊዜ በኤርትራ ኃይሎች እጅ መግባታቸውን ወንድማቸው በየነ ጴጥሮስ(ፕ/ር) ለአል ዐይን አማርኛ መናገራቸው ይታወሳል።
የሁለቱ ሀገራት ጦርነት እንደተጠናቀቀ የጦር ምርኮኞቻቸውን ሲቀያየሩ ኮሎኔሉ ግን ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ መቅረታቸው ብዙዎችን አነጋግሯል። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ኮሎኔሉ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ገፍቶ ባለመሄዱ በዛብህ ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ በኤርትራ እስር ቤት መቅረታቸውን ተቀዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች እና ሌሎችም ሲያነሱ ቆይተዋል።
የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(የሕወሓት) ነባር ታጋይ አቶ ስብሃት ነጋ ከሰባት ዓመታት በፊት “ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መሞታቸው እንደተነገራቸው ገልጸው ነበር። አቶ ስብሃት ነጋ፤ እየጠየቅን የነበረው ከሞቱም ሬሳቸውን እንዲያሳየንና የአሟሟታቸውን ምክንያት እንዲነግሩን ነው”ማለታቸው የሚታወስ ቢሆንም ቤተሰቦቻቸው ግን ይህንን የሚያረጋግጥ ነገር አለማግኘቱን በተደጋጋሚ ተናገረዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ በተደረገው የአመራር ለውጥ ምክንያት የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ወደ ሰላም በመቀየሩ ምክንያት ጉዳዩ እንደ አዲስ ሲነሳ ቢቆይም ከአዲስ አበባም ሆነ ከአስመራ እስካሁን ስለ ኮሎኔል በዛብህ በይፋ የተባለ ነገር የለም።
በጉዳዩ ላይ ለአል ዐይን አስተያየት የሰጡት አንጋፋው ፖለቲከኛ በየነ ጴጥሮስ ወንድማቸው “በዛብህ በህይወት ላለመኖሩ በቂ ማስረጃ” አለመገኘቱን ገልጸዋል።
በህይወት አለ የሚሉ መኖራቸውን ያነሱት በየነ (ፕ/ር) አሁን ይህንን ማረጋገጥ ያለበት የኤርትራ መንግስት መሆኑን አንስተዋል። አሁን ላይ ሞቷል እያሉ የሚጽፉት ነገር የዐይን እማኞች ከሚሉት ጋር እንደሚጋጭም ነው ያረጋገጡት።
የኮሎኔል በዛብህን ጉዳይ በተመለከተ ማረጋገጥ ያለበት የኤርትራ መንግስት ነው ቢሉም በየደረጃው ያሉ የኤርትራ ባለሥልጣንት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸው ነበር።