“ወንድሜ በህይወት ላለመኖሩ በቂ ማስረጃ አልቀረበልንም”፡ በየነ ጴጥሮስ(ፕ/ር)
ሁለት ጊዜ ለኢትዮጵያ ስለተዋጉት ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ምን እየተወራ ነው?
የፖለቲከኛ በየነ (ፕ/ሮ) ወንድም ኮሎኔል በዛብህ በዉጊያ ወቅት በኤርትራ ከተያዙ በኋላ በህይወት አሉ ወይስ የሉም የሚል ድምዳሜ ላይ እስካሁን አልተደረሰም
የፖለቲከኛ በየነ (ፕ/ር) ወንድም ኮሎኔል በዛብህ በዉጊያ ወቅት በኤርትራ ከተያዙ በኋላ በህይወት አሉ ወይስ የሉም የሚል ድምዳሜ ላይ እስካሁን አልተደረሰም
በደርግ ዘመነ መንግስት የጦር አውሮፕላን አብራሪ የነበሩት የአንጋፋው ፖለቲከኛ በየነ ጴጥሮስ(ፕ/ር) ታናሽ ወንድም ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ በሕይወት አሉ ወይስ የሉም የሚለው ጉዳይ መነጋገሪያ ከሆነ አመታትን አስቆጥሯል፡፡
ኮሎኔል በዛብህ እየተዋጉ ሳለ በኤርትራ ሕዝብ ነጻነት ግምባር ሰራዊት ተይዘው ኤርትራ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ ሎንደን የሚገኘው ኤርትራ ፕሬስ የተሰኘ ድረ-ገጽ ኮሎኔል በዛብህ አስቀድሞ መሞታቸውን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሰምተዋል ማለቱን ተከትሎ ጉዳዩ እንደ አዲስ ተነስቷል፡፡
የደርግ መንግስት በ1983ዓ.ም ከወደቀ በኋላ ኮሎኔሉ ተይዘው ከነበረበት ኤርትራ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ነበር፡፡ ኮሎኔል በዛብህ ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1990ዓ.ም ወደ ጦርነት ሲያመሩ በድጋሚ የጦር አውሮፕላን አብራሪ በመሆን ጦርነቱ ላይ ዘምተዋል፡፡ አዋጊ የነበሩት ኮሎኔሉ በዚሁ ጦርነት ወቅት ያበሩት የነበረው አውሮፕላን ተከስክሶ ዘለው በጃንጥላ ሲወርዱ ለሁለተኛ ጊዜ በሻዕብያ እጅ መግባታቸውን ወንድማቸው በየነ ጴጥሮስ(ፕ/ር) ይናገራሉ፡፡
የሁለቱ ሀገራት ጦርነት እንደተጠናቀቀ የጦር ምርኮኞቻቸውን ሲቀያየሩ ኮሎኔሉ ግን ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል፡፡ ብዙዎች የዚህ ምክንያት ምንድነው ብለው ሲጠየቁ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ኮሎኔሉ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ገፍቶ ባለመሄዱ በዛብህ ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ በኤርትራ እስር ቤት መቅረታቸውን ያነሳሉ፡፡ ተቀዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችም ጭምር ይህንን ሃሳብ ሲሰነዝሩ ቆይተዋል፡፡
የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(የሕወሓት) ነባር ታጋይ አቶ ስብሃት ነጋ ከሰባት ዓመታት በፊት “ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መሞታቸው ተነግሮናል፡፡አሁን እየጠየቅን የምንገኘው ከሞቱም ሬሳቸውን እንዲያሳየንና የአሟሟታቸውን ምክንያት እንዲነግሩን ነው”ማለታቸው የሚታወስ ቢሆንም ቤተሰብ ግን ይህንን የሚያረጋግጥ ነገር አለማግኘቱ ተሰምቷል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ በተደረገው የአመራር ለውጥ ምክንያት የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ወደ ሰላም በመቀየሩ ምክንያት ጉዳዩ እንደ አዲስ ሲነሳ ቢቆይም ከአዲስ አበባም ሆነ ከአስመራ እስካሁን ስለበዛብህ በይፋ የተባለ ነገር የለም፡፡
በጉዳዩ ላይ ለአል ዐይን አስተያየት የሰጡት አንጋፋው ፖለቲከኛ በየነ ጴጥሮስ ወንድማቸው “በዛብህ በህይወት ላለመኖሩ በቂ ማስረጃ” አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡ በህይወት አለ የሚሉ መኖራቸውን ያነሱት በየነ (ፕ/ር) አሁን ይህንን ማረጋገጥ ያለበት የኤርትራ መንግስት መሆኑን አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ ሞቷል እያሉ የሚጽፉት ነገር የዐይን እማኞች ከሚሉት ጋር እንደሚጋጭም ነው ያረጋገጡት፡፡
የበዛብህን ጉዳይ በተመለከተ ማረጋገጥ ያለበት የኤርትራ መንግስት ነው ቢሉም በየደረጃው ያሉ የኤርትራ ባለሥልጣንት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል ነው ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፡፡
የኮሎኔል በዛብህ ጉዳይ የኤርትራ ባለሥልጣናት ጉዳይ ሳይሆን የኤርትራ ህዝብ ጉዳይ ነው መባላቸው ገልጸው ለምን የኤርትራ ሕዝብ ጉዳይ ነው እንደተባለ እንዳልገባቸው በየነ(ፕ/ር) አብራርተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል በዛብህን በተመለከተ የተሰጠ ምላሽ ካለ የጠየቅናቸው በየነ (ፕ/ር) የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ በደንብ መሰረት እስከሚይዝ ድረስ መጠበቅ እንደሚገባ መገለጹን ተናግረዋል፡፡