ለ20 ዓመታት በመኖሪያ ቤት ውስጥ በእንጀራ እናቱ ታግቶ የነበረው አሜሪካዊ ነጻ ወጣ
ግለሰቡ በእንጀራ እናቱ ከ11 ዓመት እድሜው ጀምሮ ታግቶ መቆየቱን ፖሊስ አስታውቋል

ፖሊስ ግለሰቡ ይህን ያህል ዓመት በምን አይነት መንገድ ያለፍቃዱ ታግቶ እንደቆየ ተጨማሪ ማጣሪያዎችን እያደረገ ነው
ለ20 ዓመታት በመኖሪያ ቤት ውስጥ ታግቶ የቆየው አሜሪካዊው የኬኔቲኬት ነዋሪ ታሪክ በመገናኛ ብዙሀን ዘንድ ሰፊ ትኩረትን አግኝቷል፡፡
በእንጀራ እናቱ ያለ ፍቃዱ ታግቶ ለሁለት አስርተ ዓመታት ከመኖሪያ ቤት ውስጥ ታስሮ የሰነበተው ግለሰብ የመኝታ ቤቱን በእሳት በማቀጣጠል አደጋውን ለመቆጣጠር በመጡ የአሳት አደጋ ሰራተኞች ነጻ ወጥቷል፡፡
የእሳት አደጋውን ተከትሎ የዋተርበሪ የፖሊስ እና የእሳት አደጋ አባላት ወደ አካባቢው ሲያቀኑ የዚህን ወጣት ልብ የሚሰብር ታሪክ ሰምተዋል፡፡
ድርጊቱን ፈጽማለች የተባለቸው እንጀራ እናት የ56 አመት ግለሰብ ስትሆን ፖሊስ በጭካኔ እና በአፈና ክስ ከፍቶባት ምርመራ እያደረገ ይገኛል፡፡
አስርተ ዓመታትን በእስር ላይ የሰነበተው ግለሰብ ከ11 አመቱ ጀምሮ እንጀራ እናቱ ያለፍቃዱ አስራ በአንድ ክፍል ውስጥ ታኖረው እንደነበር ተናግሯል፡፡
እንጀራ እናቱ ይህን ድርጊት ለምን እንደፈጸመች የሚታወቅ ነገር ባይኖርም በእነዚህ አመታት ውስጥ ለአንድ ቀን ሆስፒታል ሄዶ እንደማውቅ ፣ ጎረቤቶቹ እና ቤተሰቦቹ በህይወት እንዳለ እንኳን እንደማውቁ ለፖሊስ ተናግሯል፡፡
“ከ11 አመቴ ጀምሮ የማመልጥበትን መንገድ እና ነጻነቴን ማግኘት እፈልግ ነበር፤ ነገር ግን ሁኔታዎች በሙሉ ምቹ አልነበሩም በመጨረሻም የመጣልኝ ሀሳብ ቤቱን በእሳት ማቀጣጠል ከዛም ወይ በእሳት አደጋ ሰራተኞች መትረፍ አልያም መሞት የሚል ወሳኔ ነበር” ሲል ይናገራል፡፡
ፖሊስ ባደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ግለሰቡ ለረጅም ጊዜ በርሀብ ፣ ድብደባ እና ሌሎች ኢሰብአዊ እንግልቶች ተጎጂ ሆኖ መቆየቱን አረጋግጧል፡፡
የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ፈርናንዶ ስፓግኑሎ በሰጡት መግለጫ "ይህ ተጎጂ ከ20 አመታት በላይ የተቀበለው ስቃይ በጣም አሳዛኝ እና ሊታሰብ የማይችል ነው" ብለዋል።
ድርጊቱን በመፈጸም የተወነጀለችው ኪምበርሊ ሱሊቫኒ የተባለችው ግለሰብ በጥቃት፣ በጠለፋ፣ በጭካኔ እና በግዴለሽነት ለአደጋ በማጋለጥ ተከሳለች።
ግለሰቧ የቀረበባትን ክስ ስትሰማ መደንገጧን እንዲሁም ክሱ ከእውነት የራቀ ነው ስትል በጠበቃዎቿ በኩል ምላሽ ሰጥታለች፡፡
በትላንትናው ዕለት ጉዳዩን መከታተል የጀመረው ፍርድ ቤት ግለሰቧ ከእስር ለመለቀቅ የ300 ሺህ ዶላር ዋስ እንድታቀርብ ወስኗል፡፡