በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ዳግም ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ሊቆም እንደሚገባ የአሜሪካና አውሮፓ ዲፕሎማቶች አሳሰቡ
የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ከአፍሪካ ቀንድ ተሻግሮ ለቀይ ባህር ቀጠና ስጋት እንደሚሆንም አንስተዋል

ዲፕሎማቶቹ በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታም አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ዳግም ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ሊቆም እንደሚገባ የአውሮፓ እና የአሜሪካ የቀድሞ ዲፕሎማቶች አሳስበዋል፡፡
በጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ ምክትል ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ፓይተን ኖፍ እና የቀድሞው የአውሮፓ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ተወካይ እና በአሁኑ ወቅት የቀይ ባህር የጥናት ማዕከል ሊቀመንበር የሆኑት አሌክሳንደር ሮንዶስ በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል የሚታየውን ውጥረት አስመልክተው ፎሬይን ፖሊሲ መጽሔት ላይ ሀሳባቸውን አስፍረዋል፡፡
በ2022 መገባደጃ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ሀይሎች የጦርነት ማቆም ስምምነት ከተፈራረሙ በመጋቢት አጋማሽ ሁለተኛ አመቱን ይይዛል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የጦርነት ማቆም ስምምነት ብዙም ሳይቆይ፤ በህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶክተር) በሚመራው ቡድን እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል የተፈጠረው ክፍፍል እየተባባሰ ይገኛል፡፡
ከሶስት ቀናት በፊት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ከደብረፂዮን ቡድን ጋር በመመሳጠር በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ አሲረዋል በማለት የከሰሷቸውን ሶስት ከፍተኛ የጦር አዛዦች ከስልጣናቸው እንዲነሱ ትዕዛዝ መስጠቱን ዲፕሎማቶቹ በጽሁፋቸው ዳሰዋል፡፡
አለም በሰፊ አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ ስርዓት አልበኝነት እየተናጠች በምትገኝበት በዚህ ወቅት በትግራይ ያለው የፖለቲካ እና የጸጥታ ሁኔታ መበላሸት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ጦርነትን ሊያስከትል እንደሚችልም አሳስበዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በዛሬው ዕለት የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አንዳንድ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው እናውቃለን ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
እንዲህ ያለው ሁኔታ የሱዳንን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ ጦርነት እና ግጭቶችን በማባባስ እንዲሁም ተጨማሪ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ አለም አቀፍ ሰደድ እሳት ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ዲፕሎማቶቹ ተናግረዋል።
በባህረ ሰላጤው ሀገራት ቀይ ባህርን ለመቆጣጠር የሚደረገው ፉክክር በአፍሪካ ቀንድ ሁኔታዎች ላይ የራሱን የሆነ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል፡፡
በትግራዩ ጦርነት ወቅት የኤርትራ መንግስት መሳተፉ ቢገለጽም በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ላይ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት እንደ አንድ ፈራሚ አካል አልተሳተፈም፡፡
በሁለቱ ዲፕሎማቶች ጽሁፍ መሰረትም ከዚህ ጊዜ በኋላ በአዲስ አበባ እና አስመራ መካከል አለመተማመን እና ጥርጣሬ ሰፍኗል፡፡
አዲስ አበባ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በማፍረስ፣ ትግራይን በማተራመስ እና በሌሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋለች በሚል በአስመራ ላይ ወቀሳ ስታቀርብ፤ ኤርትራ በበኩሏ የኢትዮጵያ በቀይ ባህር ወደብ ላግኝ ጥያቄ በአሰብ እና ምጽዋ ወደብ ላይ አዛዥ ለመሆን ከመፈለግ የመነጨ ነው ትላለች።
በሁለቱም በኩል ያሉ የቃላት ምልልሶች እና የጦርነት ዝግጅቶች በሀገራቱ መካከል ጦርነት ሊያስከትል እንደሚችል አመላካች ናቸው ተብሏል፡፡
በመሆኑም በትግራይ በሚገኘው ክፍፍል የሚፈጠረው የእርስ በእርስ ግጭትም ሆኖ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል የሚከሰት ጦርነት በአካባቢው ብቻ ተወስኖ እንደማይቀር ዲፕሎማቶቹ አስጠንቅቀዋል፡፡
ሱዳን በእርስ በእርስ ጦርነት እየተናጠች ነው፤ ሶማሊያ ከአልሸባብ እና ከሌሎች አካራሪ ሀይሎች ጋር በምታደርገው ጦርነት ለብቻዋ የጸና መንግስት ማስተዳደር ተስኗታል፤ ከኤርትራ የባህር ዳርቻ 289 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የየመኑ ሀውቲ በቀይ ባህር ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ቀጥሏል፡፡
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ፍጥጫ ወደ ጦርነት የሚያድግ ከሆነ ሰሜን ምስራቅ አፍሪካን እና በጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታው ወሳኝ የሆነውን ቀይ ባህር ላይም ችግር ሊጋርጥ ይችላል።
በመሆኑም በአካባቢው እና ባህሩ ላይ ፍላጎት ያላቸው የባህረ ሰላጤው ሀገራት እና አሜሪካ ይህ ከመሆኑ በፊት ጣልቃ በመግባት ፍጥጫው የሚበርድበትን መንገድ እንዲፈልጉ የአሜሪካ እና የአውሮፓ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች አሳስበዋል፡፡