በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት “ብሄራዊ ክህደት ተፈፅሞብናል” አለ
“ሶስተኛ ወገን ትግራይ ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የሚያደርገው ጥሪ የፕሪቶሪያውን ስምምነት አደጋ ውስጥ የሚከት ነው” ብሏል

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግለት ጠይቋል
በደብረጺዮን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት “ብሄራዊ ክህደት ተፈፅሞብናል” ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩን ከሰሰ።
በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት ዛሬ ጠዋት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ “የተወሰኑ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አመራሮች ከተልዕኳቸው ወጥተው የውጪ ሃይሎች መሳሪያ በመሆን የትግራይ ህዝብን ብሄራዊ ጥቅም አሰልፈው እየሰጡ ነው” ብሏል።
በተጨማሪም “የትግራይ ሕገ-መንግስትን በመጣስ በክልሉ ህግና ስርዓትን በማፍረስ ማቆሚያ የሌለው አደገኛ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው" ሲል ከሷል።
“አሁን ደግሞ ሰራዊቱ ያለ መሪ በማስቀረት ሰራዊቱ አመራሮች ላይ ያነጣጠሩ በእገዳና ከሃላፊነት የማንሳት ስም ግልፅ ብሄራዊ ክህደት ተፈፅሟል” ብሏል በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት በመግለጫው።
“አራት የሰራዊቱ ከፍተኛ ኣመራሮች ለማገድና ለማባረር የተፃፈው ደብዳቤ ከሃላፊነት ውጪ የተደረገና ተፈፃሚነት የሌለው መሆኑ ኣሁንም በግልፅ ሊታወቅ ይገባል” ብሏል።
መግለጫው አክሎም “ትግራይ ውስጥ የተጀመረው ህግና ስርዓት የማስከበር ስራ ደግሞ ግዚያዊ አስተዳደሩና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የሚያፈርስ ሳይሆን የተጀመረውን የሰላም ስምምነት ትግበራ ይበልጥ የሚያጠናክር ነው” ሲል ገልጿል።
በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት “የክህደት ቡድን” ስል የጠራውን አካል “ሃላፊነት የጎደለው ስራውን ኣጠናክሮ በመቀጠል ህወሓትና የትግራይ ሰራዊትን ጥላሸት በመቀባትና በመወንጀል “ትግራይ ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል” በመግለፅ እያደናገረ ሶስተኛ ወገን ወደ ትግራይ እንዲገባ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ጥሪ እያደረገ ነው” ብሏል።
“ትግራይ ውስጥ ያጋጠሙት ችግሮች ለመፍታት የህወሓት፣ የህዝቡና የሰራዊቱ ውሳኔዎች መተግበር አማራጭ የሌለው ነው” ብሏል መግለጫው።
በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት በመግለጫው “የኢትዮጵያ መንግስትና የዓለም ማህበረሰብ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በሙሉነትና በፍጥነት በመተግበር ወደ ዘላቂ ሰላምና መልሶ መቋቋም በሚወስድ መንገድ አወንታዊ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብሏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትናንትናው እለት በክልሉ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግለት መጠየቁ ይታወሳል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው “ከጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ አንዳንድ የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች ከተልኮ ወጭ የአንድ ጠባብ ቡድን የስልጣን ጥም ለማርካት በማለት ግልፅ የመፈንቅለ መንግስት እንስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል” ብሏል።
“በዚህ ሳምንትም በተመሳሳይ በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ግንባር አዛዦች እንቅስቃሴው በከፋ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል” ብሏል መግለጫው።
ይህንን አደገኛ እንቅስቃሴ ለመግታት እና ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ሁሉ ለማስቆም የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ለትግራይ ጦር ዋና አዛዥ ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ትእዛዝ ቢሰጥም ማስቆም እንዳልቻለ አስታውቋል።
ሁኔታው እልባት ባለማግኘቱ የግንባሩ የጦር አዛዦች እገዳ እንደተጣለባቸው ያመላከተው መግለጫው፤ የጸጥታ ቢሮ እንዲመራ የተሾመው አካል ህግ ከመጠበቅ ይልቅ ከወንጀለኞች ጎን በመቆም መግለጫ አውጥቷል ብሏል።
ይህንን ተከትሎም የጸጥታው ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ ከኃላፊነታቸው እንደተነሱም መግለጫው አመላክቷል።
በአሁኑ ሰዓት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እየተፈፀመ መሆኑን ያስታወቀው ጊዜያዊ አስተዳሩ፤ “የመንግስ መዋቀቅርን ከላይ እስከታች የማፍረስ እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል” ብሏል።
“የትግራይ ጦር ከፍተኛ አዛዦች የኃላ ቀሩን ቡዱን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ መንግስት እንዲፈርስ እንዲሁም የፕሪቶርያ ስምምነት በይፋ እንዲጣስ በማድረግ የትግራይን ህዝብ ዳግም ወደ ሌላ የጥፋት ጦርት እያስገቡ ነው” ብሏል መግለጫው።
አስተዳሩ አክሎም “የፌደራል መንግስት በጸጥታ ሃይሎች ስም የሚንቀሳቀሱት ኋላ ቀር እና ወንጀለኛ ቡድን ተላላኪዎች መሆናቸውንና የትግራይን ህዝብና ጊዜያዊ አስተዳደር የማይወክሉ መሆናቸውን ተረድቶ አስፈላጊውን እርዳታ ሊያደርገወ ይገባል” ሲልም ጠይቋል።