ከወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች መካከል ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት እንዳሉ እናውቃለን-ጌታቸው ረዳ
አቶ ጌታቸው “አሁን ባለው ሁኔታ በትግራይ በይፋ መፈንቀለ መንግስት ስራ እየተሰራ ነው” ብለዋል

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ያቀረበው ይፋዊ ጥያቄ እንደሌለ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ “ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ከወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች መካከል ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት እንዳሉ እናውቃለን” አሉ።
አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ ወቅታው ሁኔታ ዙሪያ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው “ከትግራይ ክልል ትርምስ እናተርፋለን የሚሉ ብዙ አካላት አሉ” ያሉ ሲሆን፤ “ከዚህም ውሰጥ የኤርትራ መንግስት አንዱ ነው” ብለዋል።
“የኤርትራ መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባው ትግራይን ከካርታ ውስጥ ለማጥፋት ሲደረግ የነበረው ጦርነቱ በስምምነት በመቆሙ ነው” ሲሉም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
የኤርትራ ፍላጎት የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ መንግስትን ይወራል ብለው በሚሰጉበት ሰአት ትግራይን እንደ መሸሸጊያ መጠቀም አሊያም ጠንከር ያለ አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለው ካመኑ ከትግራይ ጋር በመሆን ወደ አዲስ አበባ ማማተር ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ጉዳይ ውስጥ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይል ወይም የፀጥታ ኃላፊ ከነሱ ጋር በማበር ለመሥራት ማሰቡ አስደንጋጭ ነው በማለትም በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው አክለውም ፤ “አሁን ባለው ሁኔታ በትግራይ በይፋ መፈንቀለ መንግስት ስራ እየተሰራ ነው” ነው ብለዋል።
አቶ ጌታቸው፤ ህጋዊ ተቀባይነት ያጣ አንድ የህወሓት ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሚና በኃይል በመንጠቅ ስልጣንን ለመቆጣጠር ያለውን ፍላጎት ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ህጋዊ ተቀባይነት ያጣው የህወሓት ቡድን በቀበሌ፣ ወረዳ እና ዞን የቢሮዎችን ማሕተም በሕገ ወጥ መንገድ እየነጠቀ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
አቶ ጌታቸው አክለውም፤ “አሁን ባለው ሁኔታ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ይፋዊ ጥያቄ አላቀረበም” ሲሉም ተናግረዋል።
“ጊዜያዊ አስተዳደሩ በፌዴራል መንግስቱና በህወሓት መካከል የተቋቋመ ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ጌዚያዊ አስተዳደሩ አደጋ ላይ ሲወድቅ እና ሰሲፈርስ የፌዴራል መንግስቱ ቆሞ ማየት የለበትም፤ እርምጃ የመውሰድ ሀላፊነት አለበት ብለዋል።
አቶ ጌታቸው፤ “በአሁኑ ሰአት ጦርነት ለማስቆም የፌዴራል መንግስቱ ከማንም በላይ ሀላፊነት አለበት” ሲሉም ተናግረዋል።
በተለይም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በአስማማኝ ሁኔታ በሁሉም ወገን እንዲተገበር እንዲሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ትግራይ ክልልን ወደ አላስፈላጊ ትርምስና ጦርነት ለመክተት የሚሞክረው የህወሓት ቡድን ከድርጊቱ ሊቆጠብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ድርጊቱን ለማስቆም የክልሉ ሕዝብ፣ የፌዴራል መንግስትና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የበኩላቸውንሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትናንትናው እለት በክልሉ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግለት መጠየቁ ይታወሳል።
አስተዳሩ በትናንቱ መግለጫው “የፌደራል መንግስት በጸጥታ ሃይሎች ስም የሚንቀሳቀሱት ኋላ ቀር እና ወንጀለኛ ቡድን ተላላኪዎች መሆናቸውንና የትግራይን ህዝብና ጊዜያዊ አስተዳደር የማይወክሉ መሆናቸውን ተረድቶ አስፈላጊውን እርዳታ ሊያደርገወ ይገባል” ሲልም ጠይቋል።
ይህንን ትከትሎም በደብረጺዮን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት “ብሄራዊ ክህደት ተፈፅሞብናል” ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩን ከሷል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግስት “አስፈላጊውን ድጋፍ” እንዲያደርግለት መጠየቁን በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት "በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሶስተኛ ወገን ትግራይ ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የሚያደርገው ጥሪ በፍፁም ተቀባይነት የለዉም" ሲል ተቃዉሟል።