ተመድ “በ2030 የዓለም የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀት መጠን 10 ነጥብ 6 በመቶ ይጨምራል” አለ
በሻርም ኤል ሼክ የሚካሄደው ኮፕ-27 ትኩረት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ስሚወሰደው እርምጃ እንደሚሆን ይጠበቃል
የበለጸጉ ሀገራት የገቡትን ቃል ባለመተግበራቸው ዓለማችን ከፍተኛ አደጋ እንደተጋረጠባት የተመድ መረጃዎች ያመለክታሉ
አሁን ባለበት ሁኔታ በ2030 የዓለም የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀቶች መጠን ከ2010 ጋር ሲነጻጸር በ10 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚጨምር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታወቀ።
የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ፓነል የሙቀት መጠን ወደ 1ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ ለማውረድ በ2030 የልቀት መጠንን 43 በመቶ መቀነስ እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል።
በመጪው ወርሃ ህዳር በግብጽ ሻርም ኤል ሼክ ከተማ ለአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ-27) የሚሰበሰቡ መሪዎች ዋና ትኩረት የበለጸጉ ሀገራት ገቡትን ቃል ተግባራዊ ስለማድረግ እንደሚሆንም ጨምር ማመላከቱ ሮይተርስ ዘግቧል።
"ባለፈው ዓመት በግላስጎው በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ሁሉም ሀገራት የአየር ንብረት እቅዶቻቸውን በድጋሚ ለማየት እና ለማጠናከር ተስማምተዋል" ሲሉም የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ዋና ጸሃፊ ሲሞን ስቲል በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
አክለውም "ከኮፕ-26 ጀምሮ 24 አዲስ ወይም የተሻሻሉ የአየር ንብረት ዕቅዶች ብቻ መቅረባቸው ተስፋ አስቆራጭ ነው" ብለዋል ዋና ጸሃፊው።
ኣዳዲስ እቅድ ይዘው ከመጡና ማሻሻያ ካደረጉ ሀገራት ቦሊቪያ፣ ቫኑዋቱ እና ኡጋንዳ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ካርበትን የሚለቁትን ህንድ እና የኢንዶኔዥያ ይገኙበታል።
የበለጸጉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የገቡትን ቃል ለመተግበር በመዘግየታቸው ዓለማችን ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባታል ሲሉ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም።
በፓሪሱ ጉበዔ የበለጸጉ ሀገራት እያደጉ ላሉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን እንዲቋቋሙ የ100 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም በቃላቸው ሊገኙ እንዳልቻሉ በተለያየ መልኩ ሲገለጽ ቆይቷል።
በዚህ ስጋት የገባቸው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ዓለም ወደ ተግባር ካልገባ የሚመጣው አደጋ ከዚህም የባሰ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የፓኪስታን አንድ ሶስተኛ ክፍል በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በአውሮፓ በ500 ዓመታት ውስጥ ያጋጠመው የበጋ ወቅት እንዲሁም መላው ኩባ እና አሜሪካ ኢያን እየደረሰ ያከው የአውሎ ነፋስ አደጋ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች ናቸው ያሉት ዋና ጸኃፊው፤ ችግሩን ለመቅረፍ የሚወሰዱ እርመጃዎች በቂ አይደሉም ሲሉም ነበር የተናገሩት፡፡
“የአየር ንብረት ትርምስ ወደፊት እየገሰገሰ ቢሆንም የሚወሰደው እርመጃ ቆሟል” ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው፤ በመጪው ህዳር ወር በግብጽ ሻርም ኤል-ሼክ ከተማ ስለሚዘጋጀው 27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን በማስመለከት ከሁለት ሳምንታት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ።
አሁን ያሉት ቃል ኪዳኖች እና ፖሊሲዎች የዓለምን የሙቀት መጠን 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ማሟላት ይቅርና ወደ 2 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ እያለ ነው ስለዚህም የነገ ህይወታችን አጠያያቂ ነውም ብለዋል።
እናም ቀጣዩ ጉባዔ (ኮፕ-27) ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ስሚወሰደው እርምጃ ቅድሚያ ሰጥተው የሚመክሩበት ወሳኝ ጉባኤ መሆን እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።