ህንድ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ግሪክ የተለየ መለዮ የሚለብሱ ወታደሮች ካሏቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ
ፈረንሳይ በዓለማችን ለየት ያለ ወታደራዊ መለዮ ካላቸው ሀገራት ተጠቃሽ ሀገር ናት፡፡
በተለይም የምህንድስና ዘርፍ ወታደሮቿ ለተዋጊ ወታደሮቿ መንገድ የሚጠርጉ እና የሚያመቻቹ ናቸው፡፡
ይህ የወታደራዊ ክፍል ትርኢት ሲያሳያ መጥረቢያ እና የብረት መምቻ ፋስ በመያዝ ወደ አደባባይ ይወጣል፡፡
ይህ የፈረንሳይ ወታደራዊ ክፍል ከፈረንጆቹ 1831 ጀምሮ በአደባባይ የትርኢት ስፍራዎች ላይ መለዮውን ለብሶ ሲወጣ የብዙዎችን ትኩረት በመሳብ ይታወቃል፡፡
ሌላኛው ለየት ያለ ወታደራዊ መለዮ የሚለብሰው ወታደር የግሪክ ሲሆን በብዛት ክብረ በዓላት ላይ ተለብሶ ወደ አደባባይ የሚወጣ ሲሆን መለዮው ግሪክ ለረጅም ክፍለ ዘመናት ከኦተማን ቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት የተከፈለውን መስዋዕትነት ለማሰብ ተብሎ መዘጋጀቱ ይገለጻል፡፡
የህንድ ድንበር ጠባቂ ወታደሮች የሚለብሱት መለዮ ደግሞ ሌላኛው ግርምት የሚያጭረው የዓለማችን ወታደራዊ መለዮ ነው፡፡
በወጣት ወታደሮች የተሞላው ይህ የህንድ ወታደራዊ ክፍል ከ1965ቱ የህንድና ፓኪስታን ጦርነት በኋላ እንደተመሰረተ የቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ ያሳያል፡፡
በወራት ውስጥ በህዝብ ብዛት ቻይናን በመብለጥ መሪ የምትሆነው ህንድ የጦር አባላቷ እጅግ በርካታ ናቸው። ይህ የሀገር ድንበር ጠባቂ ጦር ክፍል ትርኢት ሲያሳይ የወታደሮቹ ብዛት ከመለዮው ለየት ማለት ጋር ተዳምሮ ድምቀት ይፈጥራል፡፡
የፊጂ ፕሬዝዳንት ጠበቂዎች መለዮ ደግሞ ሌላኛው አግራሞትን ከሚያጭሩ ወታደራዊ መለዮዎች መካከል አንዱ ሲሆን ወታደሮቹ በተለያዩ ቀለማት የደመቁ ቁምጣ ለብሰው ትርኢት ያሳያሉ፡፡
የሞንጎሊያ ወታደሮች በሰላም ጊዜ ነጭ በጦርነት ጊዜ ደግሞ ጥቁር መለዮ የሚለብሱ ሲሆን ይህ መለዮ በሀገሪቱ ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት የነበረውን የሙጋል አገዛዝን ለማስታወስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
ሌላኛዋ የዓለማችን ለየት ያለ መለዮ ያላት ሀገር ደቡብ ኮሪያ ስትሆን ከፈረንጆቹ 1996 ጀምሮ ሮያል አርሚ የተሰኘ ወታደራዊ ክፍል አቋቁማለች፡፡
ይህ ወታደራዊ ክፍል የኮሪያ ቤተ መንግስትን በመጠበቅ የሚታወቅ ሲሆን የጎብኚዎችን ትኩረት እንደሚስብም ይነገርለታል።
የስዊዝ ቫቲካን ጥበቃ ክፍል ደግሞ ሀገሪቱ ያላትን ታሪክ ለማስታወስ ሲባል ከ1914 ጀምሮ ጥቅም ላይ የሚውል ወታደራዊ መለዮ አለው።
የብዙ ቀለማት ውጤት የሆነው ይህ መለዮ በዓለማችን ትኩረትን ከሚስቡ መለዮዎች መካከል አንዱ ነው፡፡