የትራፊክ ፖሊስ መስሎ ለወራት በጎዳናዎች ላይ ሲሰራ የቆየው ግለሰብ ታሰረ
ግለሰቡ ወደዚህ ስራ የገባው ስራ በማጣቱ እንደሆነ ለፖሊስ ተናግሯል
ግለሰቡ ልክ እንደ እውነተኛ ትራፊኮች አጥፊዎችን ሲያስተምር እና ሲቀጣ ቆይቷል ተብሏል
የትራፊክ ፖሊስ መስሎ ለወራት በጎዳናዎች ላይ ሲሰራ የቆየው ግለሰብ ታሰረ።
የ48 ዓመቱ ጎልማሳ ቪክተር ስራ ማጣት እና ቁጭ ማለት ሲመረው ትራፊክ ለመሆን ሀሳቡ ይመጣለታል።
ትራፊክ የሚያስመስለውን አልባሳት በጥንቃቄ በመግዛት ወደ ስራ የገባው ቪክተር በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ እንደልቡ እየተሽከረከረ መስራቱን ይቀጥላል።
እውነተኛ ትራፊኮች እሚያደርጉትን ሂደቶች በማጥናት ስራ የጀመረው ይህ ግለሰብ ከቋንቋ አጠቃቀም፣ አለባበስ እና ከሹፌሮች ጋር ስለሚያደርጓቸው ግንኙነቶች ሳይቀር ጥናት አድርጎ ስራውን ጀምሯል።
በድርጊቱ ትክክለኛነት ምክንያትም የትራፊክ እንቅስቃሴዎችን ቅኝት የሚያደርጉ ሀላፊዎችን ሳይቀር ያሞኘው ይህ ግለሰብ በመጨረሻም አጭበርባሪ ሰው እንደሆነ ተደርሶበታል።
በሩሲያዋ ስታቭሮፖል ክልል ነዋሪ የሆነው ይህ ሰው በራስ መተማመኑ እና ህግ አዋቂነቱ አብረውት የሚሰሩት እውነትኛ ትራፊኮች ሳይቀር እንዳይጠረጥሩት አድርጓቸዋል ተብሏል።
በድርጊቱም አጥፊ አሽከርካሪዎችን የሚያስተምርበት እና የሚቀጣበት መንገድ ጎበዝ እና ስራውን የሚያውቅ እውነተኛ ትራፊክ እንዳስመሰለውም ተገልጿል።
አጥፊ አሽከርካሪዎች የእቃ እና ገንዘብ ስጦታዎችን ሲሰጡት ለመቀበል አይኑን እያሽም የተባለው ይህ ግለሰብ በመጨረሻም እድል ፊቱን አዙራበት በመርማሪዎች እጅ ወድቋል።
ግለሰቡ አጭበርባሪ ትራፊክ መሆኑ የተነቃው የክልሉ ፖሊስ በአንድ ከተማ አራት ትራፊኮችን ብቻ አሰማርቶ ሳለ ተቆጣጣሪዎች ግን አምስት ትራፊክ ኦፊሰሮች በስራ ላይ መሆናቸውን በሲሲቲቪ ካሜራ ላይ ማስተዋላቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል።
እንዴት አምስት ትራፊኮች ስራ ላይ ተገኙ? በሚል ምርመራ ሲደረግም ቪክተር አታላይ ትራፊክ መሳይ ሰው መሆኑ ተደርሶበት ለእስር ተዳርጓል።
ለእስር የተዳረገው ይህ ግለሰብም የፖሊስን አልባሳት መልበስ፣ የትራፊክ ህክ በመተላለፍ እና በማጭበርበር ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።
ከእሱ በተጨማሪም አብረውት ሲሰሩ የነበሩ ትራፊኮች ጉዳዩን ሪፖርት ባለማድረጋቸው በወንጀል ተባባሪነት ክስ እንደቀረበባቸው ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።