ከቪዛ ነፃ የሆነ ጠንካራ ሁለተኛ ፓስፖርት ልናገኝ የምንችልባቸው 10 ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
በሀገራቱ በተወሰነ ገንዘብ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ሰዎች ያለ ቪዛ በርካታ ሀገራት የሚያስገባ ፓስፖርታቸውን ይሰጣሉ
በሀገራቱ ፓስፖርቶች ያለ ቪዛ ከ103 እስከ 192 ሀገራት መጓዝ ያስችላሉ
አፍሪካዊ ከመሆን ጋር ተያይዞ ከሚያጋጥሙን ችገሮች ውስጥ አንዱ የአፍሪካ ፓስፖርት ይዘን በምንንቀሳቀስበት ጊዜ የሚያጋጥመን የጉዞ ገደብ ነው።
በርካታ አፍሪካውያን ቪዛ መከልከል፣ ጥብቅ የጉምሩክ ሥርዓት ማለፍን ጨምሮ፣ አልፎ ተርፎም በአፍሪካ ፓስፖርታቸው ምክንያት እስከ መታሰርም ደርሰዋል።
ለዚህም መፍትሄ ሊሆን የሚችል አማራጭ ሁለተኛ ፓስፖርት መያዝ ሲሆን፤ ለዚህም ደግሞ ወደ በርካታ ሀገራት ለመግባት ቪዛ የማያስፈልጋቸው ጠንካራ የሆነ ፓስፖርታቸውን በኢንቨስትመንት አማካኝነት የሚሰጡ ሀገራት አሉ።
ሀገራቱ ከ100 ሺህ ዶላር ጀምሮ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የውጭ ሀገራት ዜጎች ፓስፖርታቸውን በነጻ እንደሚሰጡም ነው የተመላከተው።
ፓስፖርታቸውን በኢንቨስትመንት የሚያቀርቡ ሀገራትን ዝርዝር ይመልከቱ፤
1. አንቲጓ እና ባርቡዳ
የአንቲጓ እና ባርቡዳ ፓስፖርትን ለማግኘት ፓስፖርት ለማግኘት ዝቅተኛ የኢንቨስትመንት ገደብ (100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር) ሊኖረን ይገባል።
ይህንን ኢንቨስትመንት ሟሟላት የሚችል ሰው ፈጣን በሆነ የሀገሪቱ የፓስፖርት መስጫ ስርዓት አማካኝነት በቶሎ ማግኘት ይችላል። አንቲጓ እና ባርቡዳ ፓስፖርት የያዙ ሰዎች ወደ 153 ሀገራት እና ግዛቶች ከቪዛ ነፃ መጓዝ ይችላሉ።
2. ዶሚኒካ
የዶሚኒካን ፓስፖርት ለማግኘት፣ ከ200 ሺህ ዶላር ጀምሮ ባሉ የሪል እስቴት እና በ100 ሺህ ዶላር የመንግስት ቦንድ ኢንቨስትመንቶች ያሉ ተመጣጣኝ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ላይ መሳተፍ ነው የሚጠበቀው።
3. ግሬናዳ
የግሬናዳ ፓስፖርትን ለማግኘት ከ22 ሺህ ጀምሮ ባሉ እንደ ሪል ስቴት እና ሌሎች የንግድ አማራጮች ላይ ባሉ የኢንሰትምንት አማራጮች መሳተፍ ብቻ ይጠብቃል ተብሏል።
4. ሴንት ኪትስ እና ኔቪስ
ሴንት ኪትስ እና ኔቪስ ፓስፖርት በፕላቲኒየም ፓስፖርትነት የሚገለጽ ሲሆን፤ ይህንን ፓስፖርት ያዘ ማንኛውም ሰው ወደ 155 ሀገራትና ግዛቶች ያለ ቪዛ በነጻት መንቀሳቀስ ይችላል። ታዲያ ይህንን ፕላቲኒየም ደረጃ ፓስፖርት ለማግኘት ከ250 ሺህ ዶላር ጀምሮ ኢንቨስት ማድረግን ይጠይቃል።
5. ሴንት ሉቺያ
የሴንት ሉቺያ ፓስፖርት የያዘ ማንኛውም ሰው ወደ 155 ሀገራትና ግዛቶች ያለ ቪዛ በነጻት መንቀሳቀስ ይችላል። ይህንን ፓስፖርት ለማግኘት የሚጠበቅብን ከ300 ሺህ ዶላር ጀምሮ በሀገሪቱ የሪል ስቴት ወይም የመንግስት ቦንድ ኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ መሳተፍ ነው።
6. ኦስትሪያ
የኦስትሪያ ፓስፖርት የያዘ ማንኛውም ሰው ወደ 192 ሀገራትና ግዛቶች ያለ ቪዛ በነጻት መንቀሳቀስ ይችላል። ይህን ፓስፖርት ለማግኘት ትንሽ ወደድ ይላል የተባለ ሲሆን፤ እስከ 8 ሚሊየን ዩሮ በሀገሪቱ ኢንቨስት ማድረግ ፓስፖርቱን ያስገኛል። የኦስትሪያ ፓስፖርት በሁሉም የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ውስጥም የመንቀሳቀስ መብትን ያጎናጽፋል።
7. ፖርቹጋል
በዓለምችን ላይ ካሉ ጠንካራ ፓስፖርቶች ውስጥ የፖርቹጋል ፓስፖርት አንዱ ሲሆን፤ የፖርቹጋልን ፓስፖርት የያዘ ማንኛውም ሰው ወደ 191 ሀገራትና ግዛቶች ያለ ቪዛ በነጻት መንቀሳቀስ ይችላል።
ከ500 ሺህ ዶላር ጀምሮ በሪል ስቴት ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ የፖርቹጋልን ወርቃማ ፓስፖርት የሚያስገኝ ሲሆን፤ ከ5 ዓመት በኋላም የሀገሪቱን ዜግነት ያስገኛል ተብሏል።
8. ግሪክ
የግሪክን ፓስፖርት ለማግኘት እስከ 250 ሺህ ድረስ በሪል ስቴት ላይ ኢንቨስት ማድረግን የሚጠይቅ ሲሆን፤ በዚህም ከ7 ዓመት በኋላ ዜግንት የሚያስገኝ ነው።
9. ሞንቴኔግሮ
የሞንቴኔግሮ ፓስፖርት ለማግኘት ከ250 ሺህ ዩሮ ጀምሮ ኢንቨስት ማድረግ የሚተይቅ ሲሆን፤ ይህም ከስድስት ዓመታት በኋላ ዜግነት የሚያስገኝ ነው።
10. ቫኑአቱ
የቫኑአቱ ፓስፖርትን የያዙ ሰዎች ወደ 103 ሀገራትና ግዛቶች ያለ ቪዛ በነጻት መንቀሳቀስ ይችላል። ይህንን ፓስፖርት ለማግኘትም በሀገሪቱ 130 ሺህ ዶላር ጀምሮ ኢንቨስት ማድረግን ይጠይቃል።