እጽዋት እንደ ሰው ልጅ ውስጣዊ ስአት እንዳላቸው ያውቃሉ?
የሰው ልጅ በቀን ወይም በምሽት ሊያደርጋቸው የሚገቡ ጉዳዮችን የሚቆጣጠር እና የሚያዝ ውስጣዊ ስአት ወይም “ቦዲ ክሎክ” አለ
በእንግሊዝ የሚገኘው የሁል ዩኒቨርሲቲም እጽዋት እንደ ሰው ልጅ እንቅስቃሴያቸው የሚመራው በውስጣዊ ስአታቸው መሆኑን አረጋግጧል
ከረጅም የአውሮፕላን ጉዞ በኋላ የሚገጥም ችግር “ጄት ላግ” ይሰኛል።
መነሻችን ቀን ሆኖ መዳረሻችን ሀገርም እንዲሁ ቀን ከሆነ ሰውነታችን እንቅልፍ እንዲወስደን ያዛል፤ የደረስንበት ቦታ ላይ ግን ሩጫ የበዛበት ቀን ይሆንና መተኛት ሳይፈቅድልን ሲቀር ሰውነታችን እና የውጭው አለም ይጣላሉ።
ይህ እረፍት እንድንወስድ የሚያዘው የሰውነታችን ውስጣዊ ስአትም “ቦዲ ክሎክ” ወይም “ሲርካዲያን ክሎክ” ይባላል።
በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶችም እጽዋት፣ ፈንገስና የተወሰኑ ባክቴሪያዎች ጭምር የራሳቸው ውስጣዊ ስአት እንዳላቸውና የሰውን ልጅ ባህሪ እንደሚጋሩ ያሳያሉ።
ምንም እንኳን እጽዋት እንደሰው ልጅ ረጅም አለምአቀፍ በረራን ባያደርጉም ለረጅም ስአት ከተለመደው ኡደታቸው የሚገታ ነገር ሲገጥማቸው ውስጣዊ ስአታቸው ተቃውሞውን እንደሚገልጥ የሁል ዩኒቨርሲቲ ጥናት አሳይቷል።
ጥናቱ እጽዋት የስነህይወታዊ ኡደት ከሰው ልጅ ጋር የሚያመሳስለው ነገር እንዳለ ማረጋገጡን የጥናቱ ዋና መሪ ካትሪን ሀበርድ ይናገራሉ።
እጽዋት እንደ ሰው ልጅ በውስጣቸው እረፍት የማድረግም ሆነ ሌላ ተግባር የሚከውኑበት ውስጣዊ ወይም ባዮሎጂካል ስአት አላቸው የሚለው ጥናቱ፥ በቀጣይ በዚሁ ዘርፍ ላይ ለሚደረጉ ምርምሮች በር ከፋች ነው ተብሏል።
የእጽዋትን ባዮሎጂካል ስአት መረዳት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመቅረፍ መፍትሄ እንደሚሆንም ነው ሀበርድ የሚገልጹት።
እጽዋት ውስጣዊ ስአት እንዳላቸው ለመጀምሪያ ጊዜ የተረጋገጠው በግሪክ ነው፤ አንድ መርከበኛ ስአት ጠብቆ ቅጠሉን የሚዘረጋውና የሚሰበስበውን የታምሪድ ዛፍ በየቀኑ ተከታትሎ ጥናቱን ይፋ ካደረገ በኋላ።
ፈረንሳዊው ጀከስ ዶርቱስ ደ ማይረንም በ18ኛው ክፍለዘመን ያደረገው ሳይንሳዊ ምርምርም እጽዋት ስአት ጠብቀው ቅጠላቸውን ሲዘረጉና ሲያጥፉ እንዲሁም በጨለማ ወቅት ጭምር ሲነኩ የሚያሳዩትን ምላሽ በዝርዝር አመላክቷል።
ጥናቱ የእጽዋት እንቅስቃሴ በብርሃን እና ጨለማ ሳይሆን በራሳቸው ውስጣዊ ስአት ወይም “ባዮሎጂካል ክሎክ” እንደሚመራ ያረጋገጠ ነበር።
አዲሱ የሁል ዩኒቨርሲቲ ጥናትም የእጽዋትን ከሰው ልጅ የሚቀራረብ ህይወት የሚያሳይ ነው ተብሏል።