በትግራይ ክልል በጦርነቱ "በእያንዳንዱ ቤት" የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ የሚያሳይ ጥናት ሊወጣ ነው
ሁሉንም ያካተተ ነው የተባለው ጥናቱ በትግራይ የደረሰውን አጠቃላይ ውድመት በአሃዝ የሚያሳይ ነው ተባለ
ጥናቱ የሰሜኑን ጦርነት ጉዳት ትክክለኛ ቁጥር ያወጣል ተብሏል
በትግራይ ክልል ጥቅምት 24፤ 2013 ዓ.ም. የተጀመረው ጦርነት ወደ ሌሎች ክልሎችም ተዛምቶ ከፍተኛ ቀውስ አስከትሏል። እስካሁን ሰብዓዊ ቀውሱን የሚገልጽ መረጃ በመንግስት በኩል ይፋ ባይደረግም፤ ቁሳዊ ውድመቱና ኪሳራው ግን 28 ቢሊዮን ዶላር (አንድ ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ብር ገደማ) መሆኑ ተነግሯል።
መንግስት በቅርቡ የጦርነቱ ማዕከላት የነበሩትን ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎችን ጨምሮ በሌሎች ሦስት ክልልሎች ለመልሶ ግንባታ የሚሆን የ20 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እቅድ መንደፉን አሳውቋል።
በትግራይ ክልል አጠቃላይ ውድመቱን በቁጥር የሚገልጽ ጥናት እያደረገ መሆኑን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለአል ዐይን አማርኛ አሳውቋል። ጥናቱ በእያንዳንዱ አባወራ ቤት የደረውን ሰብዓዊ ቀውስ ጨምሮ በክልሉ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት የሚያካትት እንደሆነ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የማህበራዊ ልማት ሽግግር ካቢኔ ሰክሬታሪያት ኃላፊ ክንደያ ገ/ሂወት (ፕ/ር) ተናግረዋል።
“ምንድን ነው የጠፋው? ሁላችንም ስለ አጠቃላይ ውድመት እናወራለን። ግን ደግሞ በቁጥር ደረጃ ምን ምን ነው የደረሰው የሚለውን ሙህራን እያጠኑት ያለ፤ ሁሉንም የሚያካትት በቅርቡ ይፋ የሚሆን ጥናት አለ” ብለዋል።
ጥናቱን በክልሉ ም/ቤት የተቋቋመው የትግራይ መርማሪ ኮሚሽን (ኢንኳየሪ ኮሚሽን) እያካሄደው መሆኑንም ተናግረዋል። የኮሚሽኑ አባላት በዋናነት የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ሙህራን መሆናቸውን የጠቆሙት ክንደያ ገ/ሂወት (ፕ/ር)፤ የጥናቱ ውጤት በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።
“በእያንዳንዱ ቤት” ከደረሰው ውድመት ይጀምራል የተባለው ጥናቱ ውድመቱን በአሀዝ እንደሚያሳይ ተጠቁሟል።
“ቤት ለቤት የተደረገ ጥናት ነው። [በዓለም አቀፍ ተቋማት] የሚጠቀሱ ቁጥሮች አሉ። ግን ጥናቱ በጣም ትክክለኛ የሆነውን ቁጥር ያወጣል። አሁን ላይ ቁጥር መናገር ባልችልም መጨረሻ ላይ የሚጣው ቁጥር ሁላችንንም የሚያስማማ ይሆናል። እኛን ብቻ ሳይሆን ዓለምም ሊቀበለው የሚችል ሜትዲዮሎጂካሊም የተመዘነ ጥናት ነው” በማለት ክንደያ ገ/ሂወት (ፕ/ር) አብራርተዋል።
“ሁሉንም ያካተተ” ያሉት ጥናት ሲወጣ ወደ መልሶ ግንባታ እንደሚገባ ተናግረዋል።
መንግስት በቅርቡ ይፋ ያደረገው የ20 ቢሊዮን ዶላር የመልሶ ግንባታ እቅድ ከክልሉ ግብዓት መውሰዱን የገለጹት ኃላፊው፤ በክልሉ የተካሄደውና የውድመቱን ስፋትና ልክ የሚያሳየው ጥናት መውጣት ለመልሶ ግንታው መሰረት መሆኑን ጠቁመዋል።
መልሶ ግንባታው ትልቅ ኃብት እንደሚፈልግም ጠቅሰው፤ ከኃብት በላይ ግን “ትልቅ መግባባት” ያስፈልጋል ሲሉ አስምረዋል።
“የምንሰማው ጥፋት የማከፋፈል ነገር አለ። ጥፋት አይከፋፈልም። የጠፋ ነገር የጠፋ ነው። ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ ያለው ስራ ነው የሚያስፈልገው። በአብዛኛው በራሳችን እዚህም ያለን፣ የትግራይ ተወላጆች የምንሰራው ስራ አለ፤ በፌደራል መንግስትም የሚሰራ አለ፤ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሁሉንም አሳትፈን ወደ ዳግም ግንባታ ነው የምንገባው” ብለዋል።