ፖለቲካ
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉና የፌደራል መንግስት የእርዳታ እህል ዘርፈዋል አለ
በዝርፊያው ምክንያት ረድኤት ድርጅቶች እርዳታ ማሰራጨታቸውን አቋርጠዋል
በዝርፊያ የተሳተፉ 186 ተጠርጣሪዎችን መለየታቸው ተነግሯል
በትግራይ ክልል በተካሄደው የምግብ እህል ስርቆት የክልሉ እና የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም የኤርትራ ወታደሮች ተሳትፈዋል ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል።
- የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትና ተመድ ለትግራይ ክልል የሚሰጡትን የምግብ እርዳታ አቆሙ
- ኢትዮጵያና አሜሪካ ከተቸገሩ ሰዎች ተነጥቋል የተባለውን የምግብ እርዳታ እየመረመርን ነው አሉ
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) በትግራይ ክልል ለተጎጂዎች የተባለ ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ ተዘርፏል ማለታቸው ይታወሳል።
በዚህም ረዲኤት ድርጅቶቹ እርዳታቸውን ባለፈው ወር አቋርጠዋል።
ሁለቱ ኤጀንሲዎች በተመሳሳይ ምክንያት ባለፈው ሳምንት በመላው ኢትዮጵያ የምግብ እርዳታን አግደዋል።
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ኃላፊ ጀነራል ፍሰሃ ኪዳኑ ለትግራይ ቲቪ እርሳቸው በመሩት ምርመራ በርካታ ሰዎች በዝርፊያ እጃቸው አለበት ብለዋል።
ኃላፊው እንዳሉት ከ860 ኪሎ ግራም በላይ ስንዴ እና 215 ሽህ ሊትር የምግብ ዘይት በክልሉ አካላት መሰረቁ ተረጋግጧል።
መርማሪዎች በዝርፊያ የተሳተፉ 186 ተጠርጣሪዎችን ለይተው ሰባቱን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውም ተነግሯል።
የተፈጸሙን ዝርፊያ እንደሚመረምር ገልጾ የነበረው የፌደራል መንግስት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስላወጣው የምርመራ ውጤት እስካሁን ያለው የለም።