የምርጫ ቦርድ ውሳኔ "የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን" ነው ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቃወመ
ህወሓት ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበለው አስታወቀ
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የቦርዱን ውሳኔ የሰላም ስምምነቱ ዋና ባለቤት የሆነውን ህወሓትን ህልውና የሚያሳጣ ነው ሲል ተቃውሟል
የትግራይ አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ምርጫ ቦርድ በህወሓት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ተቀባይነት የለውም ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ "ኃይልን መሰረት ባደረግ የአመጽ ተግባር ላይ ተሳትፏል" በማለት ከህጋዊ ፖርቲነት ለሰረዘው ህወሓት ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል የህግ አግባብ የለም ማለቱ ይታወሳል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ የቦርዱን ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው እና የሰላም ስምምነቱ ዋና ባለቤት የሆነውን ህወሓትን ህልውና የሚያሳጣ ነው ሲል ተቃውሟል።
"ውሳኔው የሰላም ስምምነቱ ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ ህወሓትን ወክለው በትግራይ አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር እየተሳተፉ ያሉት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች እውቅናን በመንፈግ የጊዚያዊ አስተዳደሩ ህልውና አደጋ ላይ ይሚጥል እንዲሁም አጠቃላይ የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን ነው" ብሏል ጊዜያዊ አስተዳደሩ።
ውሳኔው የሰላም ሂደቱን የሚያደናቅፍ እና በትግራይ የተመሰረተውን አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር አደጋ ላይ የሚጥል ነው ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ቦርዱ ውሳኔውን እንዲያስተካክል ጠይቋል።
ፖርቲው ህወሓትም ባወጣው የተቃውሞ መግለጫ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ህወሓትን ከአሸባሪነት መዝገብ መሰረዙን በአዎንታ የጠቀሰ ሲሆን የቦርዱ ውሳኔ "የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የማይቀበል እና እየጠነከረ በመሄድ ላይ ያለውን የስምምነቱን ትግበራ ባለቤት አልባ የሚያደርግ" ስለሆነ ተቀባይነት የለውም ብሏል።
ቦርዱ ህወሓትን ለመሰረዝ ምክንያት የነበረው በአመጽ ተግባር የመሳተፍ ሁኔታ በኘሪቶሪያው የህወሓት እና የፌደራል መንግስት ስምምነት ቢቀየርም፣ ህጋዊ ስውነት ለመመለስ የሚያስችል ህግ አለመኖሩን ገልጿል።
ቦርዱ ህወሓት ህጋዊ ሰውነት የሚያገኘው በድጋሚ ለመመዝብ ጥያቄ ሲያቀርብና ቦርዱም ሲፈቅድ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።