ሉዊስ ሱዋሬዝ ከብሄራዊ ቡድን እራሱን ማግለሉን አስታወቀ
ኡራጋዊው የ37 አመት አጥቂ ለብሄራዊ ቡድኑ በተሰለፈባቸቸው 142 ጨዋታዎች 69 ጎሎችን አስቆጥሯል
በአሁኑ ወቅት ከቀድሞ የቡድን አጋሩ ሜሲ ጋር ለኢንተር ማያሚ እየተጫወተ ይገኛል
ታዋቂው ኡራጓያዊው ሉዊስ ሱዋሬዝ ከብሄራዊ ቡድን እራሱን ማግለሉን አስታወቀ።
በሊቨርፑል እና ባርሴሎና ቤት ብቃቱን በማሳየት በአውሮፓ እግርኳስ ውስጥ ስማቸው ከሚጠራ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሉዊስ ሱዋሬዝ ከብሄራዊ ቡድን እራሱን አግልሏል፡፡
የ37 አመቱ ዩራጋዊው እግር ኳስ ተጫዋች በብሄራዊ ቡድን ተሰልፎ መጨወት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ድንቅ ብቃቱ ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆን ችሏል፡፡
በትላንትናው እለት ከብሄራዊ ቡድኑ ራሱን ማግለሉን ያስታወቀው ሱዋሬዝ በመጪው ቅዳሜ ለ2026ቱ የአለም ዋንጫ ማጣርያ ከፓራጓይ ጋር ሀገሩ በምታደርገው ጨዋታ የመጨረሻ አገልግሎቱን እንደሚሰጥ ተናግሯል፡፡
ተጫዋቹ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ “እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ በተደጋጋሚ አስቢያለሁ፤ በመጨረሻም ከብሄራዊ ቡድኑ ራሴን ለማግለል ይህ ትክክለኛው ጊዜ ይመስለኛል” ብሏል፡፡
ሱዋሬዝ አክሎም “በ19 አመቱ ለሀገሩ መሰለፍ የጀመረው ወጣት አሁን ላይ ሽማግሌ ሆኗል በብሄራዊ ቡድኑ ባሳለፍኩት ጊዜ ሁሌም ደስተኛ ነኝ” ነው ያለው፡፡
ከ17 አመት በፊት በ2007 ለመጀመርያ ጊዜ ለኡራጋይ ብሔራዊ ቡድን መሰለፍ የቻለው ተጫዋቹ በ142 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 69 ግቦችን በማስቆጠር የዩራጋይ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡
በ9 አለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ መሳተፍ የቻለ ሲሆን በ2010 የደቡብ አፍሪካ የአለም ዋንጫ ጋናን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ከማለፍ የከለከልችው በእጁ ባወጣት ኳስ ይታወሳል፡፡
ጋናዊው ተጫዋች አሳሙዋ ጂያን ወደ ጎል የመታትን ኳስ በእጁ ያዳነው ስዋሬዝ ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቶ ሀገሩ ከ40 አመታት በኋላ በአለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜን እንድትቀላቀል አስተዋጽ ነበረው፡፡
ከዚህ ባለፈም የ2011ዱ ኮፓ አሜሪካ ዋንጫን ኡራጋይ ማንሳት እንደትችል በውድድሩ በአጠቃላይ አራት ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡
በ2014 የአለም ዋንጫም በእንግሊዝ ላይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑ ከምድቡ እንዲያልፍ ሱዋሬዝ ትልቅ አብርክቶ ነበረው፡፡
በአትሌቲኮ ማድሪድ ፣ ባርሴሎና እና ሊቨርፑል ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የቻለው ሉዊስ ስዋሬዝ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ሊግ ለኢንተር ማያሚ ከቀድሞው የቡድን አጋሩ ሊዮኔል ሜሲ ጋር እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ሱዋሬዝ ብሄራዊ ቡድኑን ጨምሮ ለተለያዩ ክለቦች በአጠቃላይ ባደረጋቸው 800 ጨዋታዎች 495 ግቦችን በስሙ ማስመዝገብ ችሏል፡፡