ኡጋንዳ እና ዲ.አር ኮንጎ በኤ.ዲ.ኤፍ አማጺ ቡድን ላይ “ስኬታማ”ጥቃት መሰንዘራቸውን አስታወቁ
የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች (ADF) አማጺ ቡድን በኡጋንዳ ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀ መሆኑ ይታወቃል
የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ፍላቪያ ባይክዋሶ፤ ወታደራዊ ጥቃቱ አድማሱን እያሰፋ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል
ኡጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ በምስራቅ ኮንጎ እንደሚንቀሳቀስ በሚነገርለት የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች (ADF) አማጺ ቡድን ላይ ስኬታማ የጋራ ወታደራዊ ጥቃት መሰንዘራቸውን አስታወቁ፡፡
ከእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ጋር እንደሚተባበር በሚነገርለት ኤ.ዲ.ኤፍ ላይ የተጀመረው ጥምር ጥቃት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ፍላቪያ ባይክዋሶ ተናግረዋል፡፡
"ዒላማዎቹ በትክክል ተመተዋል፤ በአሸባሪዎች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችና ሌሎች ኢላማዎችን በምንፈልግበት ጊዜ ይቀጥላሉ"ም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ያሉት፡፡
ሀገራቱ የጋራ ወታደራዊ ጥቃት የሰነዘሩት በሰሜን ኪቩ ግዛት እና በምስራቅ ኮንጎ አዋሳኝ አካባቢዎች ነው፡፡
በውድ ማዕድናት የበለጸገችው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሄራዊ ጦር እና በስፍራው የተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር ከወራት በፊት በአማጺው ቡድን ላይ በወሰዱት እርምጃ በርካታ ታጣቂዎችን ገድለው ነበር፡፡
ከ1990ዎቹ መባቻ ጀምሮ በኡጋንዳ እና በዲ.አር ኮንጎ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች (ADF) አማጺ ቡድን በኡጋንዳ ምክር ቤት በሽብርተኝነት ተፈርጇል፡፡
አማጺ ቡድኑ ከአሁን ቀደም በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ሃገራቱ በሚጎራበቱባቸው አዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች ለደረሱ ጥቃቶች ሃላፊነት ወስዷል።
በቅርቡ በካምፓላ በሃገሪቱ ፓርላማ ፊት ለፊት የተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች በዚሁ ቡድን የተፈጸሙ ናቸው መባሉ የሚታወስ ነው፡፡
በተጨማሪም ባሳለፍነው ጥቅምት 8 እና ጥቅምት 23 በተለያዩ የካምፓላ አቅራቢያ አካባቢዎች ለተፈጸሙ ጥቃቶች ኃላፊነት መውሰዱ ይታወሳል፡፡