ሱዳን ባለመገኘቷ ምክንያት የዕለቱ የግድቡ የበይነ መረብ ስብሰባ ሳይካሄድ ቀረ
ኢትዮጵያ ባስተላለፈችው ጥሪ መሰረት የግብጽ ልዑክ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች እና ታዛቢዎች ተገኝተዋል
ስብሰባው የልዩነት እና የአንድነት ሃሳቦች የሚጠናቀሩበት ነበረ
የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት ሊያካሂዱት ታስቦ የነበረው የበይነ-መረብ ስብሰባ ሱዳን ባለመገኘቷ ምክንያት ሳይካሄድ መቅረቱን የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ ትሰበስበው የነበረው ዕለታዊ ስብሰባ ሳይካሄድ መቅረቱን በተመለከተ የፕሬስ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው ኢትዮጵያ ባስተላለፈችው ጥሪ መሰረት የግብጽ ልዑክ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች እና ታዛቢዎች ተገኝተዋል ያለ ሲሆን የልዩነት እና የአንድነት ሃሳቦችን ማጠናቀርን ታሳቢ አድርጎ የነበረው የዛሬው ስብሰባ በሱዳን አለመገኘት ምክንያት ሳይካሄድ መቅረቱን አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የሰየማቸው ባለሙያዎች ባዘጋጁት ሰነድ ላይ ያሏትን የልዩነት ሃሳቦች ለአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚ ምክርቤት ሊቀመንበር በማሳወቅ ሰነዱን ለሶስትዮሽ ድርድር እንደግብዓት ለመጠቀም መስማማቷ የሚታወስ ነው፡፡
ይኸው በኢትዮጵያ በኩል ለአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምክርቤት ሊቀመንበር ተገልጿል፡፡
ሱዳን ግን በእሷ አለመገኘት ምክንያት ስበስባው አልተካሄደም ለመባሉ ምላሽ አልሰጠችም፡፡
ትናንት የሶስቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተገኙበት የበይነ መረብ ስብሰባው መካሄዱ ይታወሳል።
ስብሰባው በደቡብ አፍሪካ የዓለምአቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት ነበር የተካሄደው።
ሚኒስትሮቹ የሕዳሴው ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ያደረጉ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ላይ በማተኮር ምክክር ተደርጓል፡፡
በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ባለሙያዎቹ የቀረጹትን ሰነድ በበጎ እንደምትመለከተው እና በቀጣይ በሚካሄደው ድርድር ሰነዱን እንደግብዓት ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡
የሱዳን ወገን በበኩሉ ሰነዱን ለሂደቱ ጠቃሚ አድርጎ እንደሚመለከተው እና በቀጣይ የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ተጨማሪ ሚና ላይ ቢጋር በማጽደቅ ድርድሩን መቀጠል እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡
የግብጽ ወገን ግን ሰነዱን ጨርሶ እንደማይቀበለው ገልጿል በሚል በሚኒስቴሩ መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ደቡብ አፍሪካ የግድቡ ድርድር የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ የሊቀመንበርነት ጊዜዋ ሳይጠናናቀቅ መቋጫ እንዲያገኝ አጥብቃ ትፈልጋለች፡፡
የትናንትናውን ስብሰባ የመሩት የውጭ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትሯ ግሬስ ናሌዲ ማንዲሳ ፓንዶር (ዶ/ር) ሃገራቱ በመጪው እሁድ እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ ከተያዘለት የሶስትዮሽ ስብሰባ በፊት የልዩነት እና የስምምነት ሃሳቦቻቸውን ለይተው እንዲያስቀምጡ ጠይቀው ነበር፡፡